ዕብራውያን 6:1-12

ዕብራውያን 6:1-12 NASV

ስለዚህ ስለ ክርስቶስ የተሰጠውን የመጀመሪያ ትምህርት ትተን ወደ ብስለት እንሂድ፤ ከሞተ ሥራ ንስሓ ስለ መግባትና በእግዚአብሔር ስለ ማመን እንደ ገና መሠረትን አንጣል፤ እንዲሁም ስለ ጥምቀቶች፣ እጆችን ስለ መጫን፣ ስለ ሙታን ትንሣኤና ስለ ዘላለም ፍርድ ትምህርት እንደ ገና አንመሥርት። እግዚአብሔር ቢፈቅድ ይህን እናደርጋለን። አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን፣ ሰማያዊውን ስጦታ የቀመሱትን፣ ከመንፈስ ቅዱስ ተካፋዮች የሆኑትን፣ መልካሙን የእግዚአብሔር ቃልና የሚመጣውን ዓለም ኀይል የቀመሱትን፣ በኋላ ግን የካዱትን እንደ ገና ወደ ንስሓ መመለስ አይቻልም፤ ምክንያቱም እነርሱ ለገዛ ጥፋታቸው የእግዚአብሔርን ልጅ እንደ ገና ይሰቅሉታል፤ ያዋርዱታልም። ዘወትር በርሷ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የምትጠጣና ለሚያርሷትም ፍሬ የምትሰጥ መሬት ከእግዚአብሔር በረከትን ትቀበላለች። ነገር ግን እሾኽና አሜከላ የምታበቅል መሬት ዋጋ ቢስ ትሆናለች፤ መረገሚያዋም ተቃርቧል፤ መጨረሻዋም በእሳት መቃጠል ነው። ወዳጆች ሆይ፤ ምንም እንኳ እንደዚህ ብንናገርም፣ ከድነታችሁ ጋራ የተያያዘ ታላቅ ነገር እንዳላችሁ ርግጠኞች ነን። እግዚአብሔር ዐመፀኛ አይደለም፤ እርሱ ሥራችሁን እንዲሁም በፊትም ሆነ አሁን ቅዱሳንን በመርዳት ስለ ስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር አይረሳም። የተሰጠው ተስፋ እስኪፈጸም ድረስ እያንዳንዳችሁ እንዲህ ያለውን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን። በእምነትና በትዕግሥት የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንድትሆኑ አንፈልግም።