አብርሃም ርስት አድርጎ ወደሚቀበለው ስፍራ እንዲሄድ በተጠራ ጊዜ በእምነት ታዘዘ፤ ወዴት እንደሚሄድ ባያውቅም፣ ዕሺ ብሎ ሄደ። በባዕድ አገር እንዳለ መጻተኛ በተስፋዪቱ ምድር በእምነት ተቀመጠ፤ የተስፋውን ቃል ዐብረውት እንደሚወርሱት እንደ ይሥሐቅና እንደ ያዕቆብ በድንኳን ኖረ፤ ምክንያቱም መሠረት ያላትን፣ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠባበቅ ነበር። አብርሃም ምንም እንኳ ዕድሜው ቢገፋም፣ ሣራም ራሷ መካን ብትሆንም፣ ተስፋን የሰጠውን ታማኝ አድርጎ ስለ ቈጠረ በእምነት የልጅ አባት ለመሆን በቃ። ስለዚህ እንደ ሞተ ሰው ከሚቈጠር ከዚህ ከአንድ ሰው፣ እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛና እንደ ባሕር ዳር አሸዋ ተቈጥሮ የማያልቅ ዘር ተገኘ። እነዚህ ሁሉ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል ሳያገኙ እምነታቸውን እንደ ጠበቁ ሞቱ፤ ሆኖም ከሩቅ አይተው ሰላም አሉት፤ በዚህ ምድር ሲኖሩ መጻተኞችና እንግዶች መሆናቸውን ተገንዝበው ነበርና። እንደዚህ የሚሉት ሰዎች የራሳቸው የሆነውን አገር እንደሚጠባበቁ ያሳያሉ። ትተዉት የወጡትን አገር ቢያስቡ ኖሮ፣ ወደዚያ የመመለስ ዕድል ነበራቸው። አሁን ግን ከዚህ የሚበልጠውን ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ አላፈረም፤ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና። አብርሃም እግዚአብሔር በፈተነው ጊዜ፣ ይሥሐቅን መሥዋዕት አድርጎ በእምነት አቀረበ፤ የተስፋን ቃል የተቀበለው እርሱ፣ አንድ ልጁን ሊሠዋ ዝግጁ ነበር፤ ይህም እግዚአብሔር፣ “ዘርህ በይሥሐቅ ይጠራል” ያለለት ነበር። አብርሃም እግዚአብሔር ሙታንን ሊያስነሣ እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር፤ ይሥሐቅንም ከሞት የመነሣት አምሳያ ሆኖ አገኘው።
ዕብራውያን 11 ያንብቡ
ያዳምጡ ዕብራውያን 11
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዕብራውያን 11:8-19
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች