ሙሴ ከተወለደ በኋላ፣ ወላጆቹ መልከ መልካም ሕፃን መሆኑን ስላዩ በእምነት ሦስት ወር ሸሸጉት፤ የንጉሡንም ዐዋጅ አልፈሩም። ሙሴ ካደገ በኋላ፣ የፈርዖን የልጅ ልጅ መባልን በእምነት እንቢ አለ። ለጥቂት ጊዜ በኀጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ፣ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን መቀበል መረጠ። ከግብፅ ሀብት ይልቅ ስለ ክርስቶስ መከራን መቀበል እጅግ የሚበልጥ ሀብት መሆኑን ተገነዘበ፤ ወደ ፊት የሚቀበለውን ብድራት ከሩቅ ተመልክቷልና። የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ ግብፅን ለቅቆ በእምነት ወጣ፤ የማይታየውንም እንዳየው አድርጎ በመቍጠር በዐሳቡ ጸና። በኵሮች የሆኑትን የሚገድለው ቀሣፊ የእስራኤልን በኵር ልጆች እንዳይገድል ፋሲካን በእምነት አደረገ፤ ደምንም ረጨ። ሕዝቡ በደረቅ መሬት እንደሚኬድ ቀይ ባሕርን በእምነት ተሻገሩ፤ ግብፃውያን ግን እንደዚሁ ለማድረግ ሲሞክሩ ሰጠሙ። ሕዝቡ የኢያሪኮን ግንብ ሰባት ቀን ከዞሩት በኋላ፣ በእምነት ወደቀ። ዝሙት ዐዳሪዋ ረዓብ፣ ሰላዮቹን በሰላም ስለ ተቀበለቻቸው ከማይታዘዙት ጋር ያልጠፋችው በእምነት ነው። እንግዲህ ከዚህ በላይ ምን ልበል? ስለ ጌዴዎን፣ ስለ ባርቅ፣ ስለ ሳምሶን፣ ስለ ዮፍታሔ፣ ስለ ዳዊት፣ ስለ ሳሙኤል፣ እንዲሁም ስለ ነቢያት እንዳልተርክ ጊዜ የለም። እነዚህ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፤ በቅን ፈረዱ፤ የተሰጠውን የተስፋ ቃል ተቀበሉ፤ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፤ የእሳትን ኀይል አጠፉ፤ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፤ ከድካማቸው በረቱ፤ በጦርነት ኀያል ሆኑ፤ ባዕዳን ወታደሮችን አባረሩ። ሴቶች፣ ሙታናቸው ተነሡላቸው። ሌሎቹ ደግሞ የተሻለውን ትንሣኤ ለማግኘት ሲሉ፣ መትረፍን ንቀው ለሞት ለሚዳርግ ሥቃይ ራሳቸውን ሰጡ፤ ከዚህም ነጻ ለመውጣት አልፈለጉም። አንዳንዶቹ መዘባበቻ ሆኑ፤ ተገረፉ። ሌሎቹ ደግሞ ታስረው ወደ ወህኒ ተጣሉ፤ በድንጋይ ተወገሩ፤ በመጋዝ ለሁለት ተሰነጠቁ፤ በሰይፍ ተወግተው ሞቱ፤ እየተጐሳቈሉ፣ እየተሰደዱና እየተንገላቱ የበግና የፍየል ቈዳ ለብሰው ዞሩ፤ ዓለም ለእነርሱ አልተገባቻቸውምና። በየበረሓውና በየተራራው፣ በየዋሻውና በየጕድጓዱ ተንከራተቱ። እነዚህ ሁሉ ስለ እምነታቸው የተመሰከረላቸው ቢሆኑም፣ ከእነርሱ ማንም የተስፋውን ቃል የተቀበለ የለም፤ እግዚአብሔር ለእኛ የሚበልጥ ነገር ስላዘጋጀ፣ ያለ እኛ ፍጹማን ሊሆኑ አልቻሉምና።
ዕብራውያን 11 ያንብቡ
ያዳምጡ ዕብራውያን 11
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዕብራውያን 11:23-40
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos