ዕብራውያን 11:1-19

ዕብራውያን 11:1-19 NASV

እምነት ተስፋ ያደረግነው ነገር እንደሚፈጸም ርግጠኛ የምንሆንበት፣ የማናየውም ነገር እውን መሆኑን የምንረዳበት ነው። አባቶችም የተመሰከረላቸው በዚሁ ነው። ዓለማት በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተፈጠሩ በእምነት እንረዳለን፤ ስለዚህ የሚታየው ነገር የተፈጠረው ከሚታየው እንዳልሆነ እንገነዘባለን። አቤል ከቃየል ይልቅ የበለጠ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ። እግዚአብሔር ስለ ስጦታው በተናገረለት ጊዜ፣ እርሱ በእምነት ጻድቅ እንደ ሆነ ተመሰከረለት፤ ቢሞትም እንኳ እስከ አሁን በእምነቱ ይናገራል። ሔኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፤ “እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም”፤ ከመወሰዱም በፊት እግዚአብሔርን ደስ እንዳሠኘ ተመስክሮለታልና። ደግሞም ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሠኘት አይቻልም፤ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሁሉ እግዚአብሔር መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት። ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር እግዚአብሔር ባስጠነቀቀው ጊዜ፣ እግዚአብሔርን ፈርቶ ቤተ ሰዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት ሠራ፤ በእምነቱ ዓለምን ኰነነ፤ በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ። አብርሃም ርስት አድርጎ ወደሚቀበለው ስፍራ እንዲሄድ በተጠራ ጊዜ በእምነት ታዘዘ፤ ወዴት እንደሚሄድ ባያውቅም፣ ዕሺ ብሎ ሄደ። በባዕድ አገር እንዳለ መጻተኛ በተስፋዪቱ ምድር በእምነት ተቀመጠ፤ የተስፋውን ቃል ዐብረውት እንደሚወርሱት እንደ ይሥሐቅና እንደ ያዕቆብ በድንኳን ኖረ፤ ምክንያቱም መሠረት ያላትን፣ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠባበቅ ነበር። አብርሃም ምንም እንኳ ዕድሜው ቢገፋም፣ ሣራም ራሷ መካን ብትሆንም፣ ተስፋን የሰጠውን ታማኝ አድርጎ ስለ ቈጠረ በእምነት የልጅ አባት ለመሆን በቃ። ስለዚህ እንደ ሞተ ሰው ከሚቈጠር ከዚህ ከአንድ ሰው፣ እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛና እንደ ባሕር ዳር አሸዋ ተቈጥሮ የማያልቅ ዘር ተገኘ። እነዚህ ሁሉ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል ሳያገኙ እምነታቸውን እንደ ጠበቁ ሞቱ፤ ሆኖም ከሩቅ አይተው ሰላም አሉት፤ በዚህ ምድር ሲኖሩ መጻተኞችና እንግዶች መሆናቸውን ተገንዝበው ነበርና። እንደዚህ የሚሉት ሰዎች የራሳቸው የሆነውን አገር እንደሚጠባበቁ ያሳያሉ። ትተዉት የወጡትን አገር ቢያስቡ ኖሮ፣ ወደዚያ የመመለስ ዕድል ነበራቸው። አሁን ግን ከዚህ የሚበልጠውን ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ አላፈረም፤ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና። አብርሃም እግዚአብሔር በፈተነው ጊዜ፣ ይሥሐቅን መሥዋዕት አድርጎ በእምነት አቀረበ፤ የተስፋን ቃል የተቀበለው እርሱ፣ አንድ ልጁን ሊሠዋ ዝግጁ ነበር፤ ይህም እግዚአብሔር፣ “ዘርህ በይሥሐቅ ይጠራል” ያለለት ነበር። አብርሃም እግዚአብሔር ሙታንን ሊያስነሣ እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር፤ ይሥሐቅንም ከሞት የመነሣት አምሳያ ሆኖ አገኘው።