እግዚአብሔር ኖኅን እንዲህ አለው፤ “በዚህ ትውልድ መካከል አንተን ጻድቅ ሆነህ አግኝቼሃለሁና ቤተ ሰብህን በሙሉ ይዘህ ወደ መርከቧ ግባ። ከንጹሕ እንስሳት ሁሉ ሰባት ሰባት ተባዕትና እንስት፣ ንጹሕ ካልሆኑት እንስሳት ደግሞ ሁለት ሁለት ተባዕትና እንስት ውሰድ፤ እንዲሁም ከወፎች ወገን ሁሉ ሰባት ተባዕትና ሰባት እንስት፣ በምድር ላይ ለዘር እንዲተርፉ ከአንተ ጋራ ታስገባለህ። ከሰባት ቀን በኋላ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናብ አዘንባለሁ፤ የፈጠርሁትንም ሕያው ፍጡር ሁሉ ከምድር ገጽ አጠፋለሁ።” ኖኅም እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ አደረገ። የጥፋት ውሃ በምድር ላይ በወረደ ጊዜ ኖኅ የስድስት መቶ ዓመት ሰው ነበር። ኖኅና ወንዶች ልጆቹ፣ ሚስቱና የልጆቹ ሚስቶች ከጥፋት ውሃ ለመትረፍ ወደ መርከቧ ገቡ። ንጹሕ ከሆኑትና ንጹሕ ካልሆኑት እንስሳት፣ ከወፎችና በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጥረታት ሁሉ ጥንድ ጥንድ፣ ተባዕትና እንስት ሆነው ወደ ኖኅ መጡ፤ እግዚአብሔር ኖኅን ባዘዘውም መሠረት ወደ መርከቧ ገቡ። ከሰባት ቀንም በኋላ የጥፋት ውሃ በምድር ላይ መጣ። ኖኅ በተወለደ በስድስት መቶኛው ዓመት፣ በሁለተኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥራ ሰባተኛው ቀን፣ በዚያ ቀን የታላቁ ጥልቅ ምንጮች በሙሉ ተነደሉ፤ የሰማይ መስኮቶችም ተከፈቱ፤ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናብ ዘነበ። በዚያ ዕለት ኖኅና ልጆቹ ሴም፣ ካምና ያፌት፣ እንዲሁም ሚስቱና ሦስቱ የልጆቹ ሚስቶች ወደ መርከቧ ገቡ። ከዱር እንስሳት ከየወገኑ፣ ከቤት እንስሳት ከየወገኑ፣ በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጥረታት ከየወገናቸው፣ ከወፎችም ከየወገናቸውና ክንፍ ያላቸው ሁሉ ዐብረዋቸው ገቡ። የሕይወት እስትንፋስ ያለባቸው ፍጥረታት በሙሉ ጥንድ ጥንድ እየሆኑ ወደ ኖኅ በመምጣት መርከቧ ውስጥ ገቡ። ከሕያዋንም ፍጥረታት ሁሉ እግዚአብሔር ኖኅን ባዘዘው መሠረት ተባዕትና እንስት እየሆኑ ገቡ፤ ከዚያም እግዚአብሔር ከውጭ ዘጋበት። የጥፋት ውሃም ለአርባ ቀናት ያለ ማቋረጥ በምድር ላይ ዘነበ፤ ውሃው እየጨመረ በሄደ መጠን መርከቧን ከምድር ወደ ላይ አነሣት። ውሃው በምድር ላይ በጣም እየጨመረና ከፍ እያለ ሲሄድ፣ መርከቧ በውሃው ላይ ተንሳፈፈች። ውሃው በጣም ከፍ በማለቱ፣ ከሰማይ በታች ያሉትን ታላላቅ ተራሮች ሁሉ ሸፈናቸው። ውሃው ከተራሮቹ ጫፍ በላይ 7 ሜትር ያህል ከፍ አለ። በምድር ላይ የነበሩ ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ፦ ወፎች፣ የቤት እንሰሳት፣ የዱር እንስሳት በምድር የሚርመሰመሱ ፍጥረታት፣ ሰዎችም በሙሉ ጠፉ።
ዘፍጥረት 7 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 7
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 7:1-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos