ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ልጆቹን ሁሉ አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “በኋለኛው ዘመን ምን እንደሚደርስባችሁ እነግራችሁ ዘንድ ተሰብሰቡ፤ “እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፤ ተሰብሰቡና ስሙ፤ አባታችሁ እስራኤልንም አድምጡ፤ “ሮቤል፣ አንተ የበኵር ልጄ ነህ፤ ኀይሌና የጕብዝናዬም መጀመሪያ፤ በክብር ትልቃለህ፤ በኀይልም ትበልጣለህ። እንደ ውሃ የዋለልህ ነህና እልቅና አይኖርህም፤ የአባትህን መኝታ ደፍረሃል፤ ምንጣፌንም አርክሰሃል። “ስምዖንና ሌዊ ወንድማማቾች፣ ሰይፎቻቸው የዐመፅ መሣሪያዎች ናቸው። ወደ ሸንጓቸው አልግባ፤ ጉባኤያቸው ውስጥ አልገኝ፤ በቍጣ ተነሣሥተው ሰዎችን ገድለዋል፤ የበሬዎችንም ቋንጃ እንዳሻቸው ቈራርጠዋል። እጅግ አስፈሪ የሆነ ቍጣቸው፣ ጭከና የተሞላ ንዴታቸው የተረገመ ይሁን፤ በያዕቆብ እበትናቸዋለሁ፤ በመላው እስራኤልም አሠራጫቸዋለሁ። “ይሁዳ፣ ወንድሞችህ ይወድሱሃል፤ እጅህም የጠላቶችህን ዐንገት ዐንቆ ይይዛል፤ የአባትህ ልጆች በፊትህ ተደፍተው ይሰግዱልሃል። አንተ የአንበሳ ደቦል ይሁዳ፤ ከዐደንህ የምትመለስ ልጄ፣ እንደ አንበሳ ያደፍጣል፤ በምድርም ላይ ይተኛል፤ እንደ እንስት አንበሳም ያደባል፤ ታዲያ ማን ሊቀሰቅሰው ይደፍራል? በትረ መንግሥት ከይሁዳ እጅ አይወጣም፤ የገዥነት ምርኵዝም ከእግሮቹ መካከል። ገዥነት የሚገባው እስኪመጣ ድረስ፣ ሕዝቦች ሁሉ ይታዘዙታል። አህያውን በወይን ግንድ፣ ውርንጫውንም በምርጡ የወይን ሐረግ ቅርንጫፍ ላይ ያስራል፤ ልብሱን በወይን ጠጅ፣ መጐናጸፊያውንም በወይን ጭማቂ ያጥባል። ዐይኖቹ ከወይን ጠጅ የቀሉ፣ ጥርሶቹም ከወተት ይልቅ የነጡ ይሆናሉ።
ዘፍጥረት 49 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 49
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 49:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos