በመላው ምድር እህል ባለመኖሩ ራቡ እየጸና ሄደ፤ ከዚህ የተነሣም ግብጽና ከነዓን በራብ እጅግ ተጐዱ፤ ዮሴፍ የግብጽና የከነዓን ሰዎች እህል በመሸመት የከፈሉትን ገንዘብ ሁሉ ሰብስቦ ወደ ፈርዖን ቤተ መንግሥት አስገባ። የግብጽና የከነዓን ሕዝቦችም ገንዘባቸው ባለቀ ጊዜ፣ ግብጻውያን ሁሉ ወደ ዮሴፍ ቀርበው፣ “የምንበላው እህል ስጠን፤ ገንዘባችን ዐልቆብናል፤ ዐይንህ እያየ እንዴት በራብ እንለቅ?” አሉት። ዮሴፍም፣ “ከብቶቻችሁን አምጡ፤ ገንዘባችሁ ካለቀ በከብቶቻችሁ ለውጥ እህል እሰጣችኋለሁ” አለ። ስለዚህ ከብቶቻቸውን ወደ ዮሴፍ አመጡ፤ እርሱም በፈረሶቻቸው፣ በበጎቻቸው፣ በፍየሎቻቸው፣ በከብቶቻቸውና በአህዮቻቸው ለውጥ እህል ሰጣቸው። በከብቶቻቸው ልዋጭ ባገኙት ምግብ የዚያን ዓመት ራብ እንዲወጡት አደረገ። ያም ዓመት ካለፈ በኋላ ሕዝቡ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ዮሴፍ መጥተው እንዲህ አሉት፣ “እንግዲህ ከጌታችን የምንሰውረው ምንም ነገር የለም፤ ገንዘባችን ዐልቋል፤ ከብቶቻችንንም አስረክበንሃል፤ እንግዲህ ለጌታችን የምንሰጠው፣ ከመሬታችንና ከእኛ ከራሳችን በቀር አንዳች ነገር የለም። ታዲያ፣ እያየኸን እንዴት እንለቅ? መሬታችንስ ለምን ጠፍ ሆኖ ይቅር? እኛንና መሬታችንን ውሰድና በለውጡ እህል ስጠን፤ እኛ የፈርዖን ገባሮች እንሁን፤ መሬታችንም የርሱ ርስት ይሁን፤ እኛም እንዳንሞት መሬታችንም ጠፍ ሆኖ እንዳይቀር የምንዘራው ዘር ስጠን።” ስለዚህ ዮሴፍ የግብጽን ምድር ሁሉ ለፈርዖን ገዛለት፤ ራቡም እጅግ ስለ ጸናባቸው ግብጻውያን ሁሉ አንዳቸውም ሳይቀሩ መሬታቸውን ሸጡ፤ ምድሪቱም የፈርዖን ርስት ሆነች። ዮሴፍም የግብጽን ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር የፈርዖን ገባር አደረገው። ሆኖም ዮሴፍ የካህናቱን መሬት አልገዛም፤ ምክንያቱም ካህናቱ ከፈርዖን ቋሚ ድርጎ ስለሚያገኙና ፈርዖን ከሚሰጣቸው ድርጎ በቂ ምግብ ስለ ነበራቸው ነው፤ ከዚህም የተነሣ መሬታቸውን አልሸጡም። ዮሴፍ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፣ ዛሬ እናንተንም መሬታችሁንም ለፈርዖን ገዝቻችኋለሁና ይህን ዘር ወስዳችሁ በመሬት ላይ ዝሩ። መከሩ በሚሰበሰብበት ጊዜ ግን ከዐምስት እጅ አንዱን ለፈርዖን ታስገባላችሁ፤ ከዐምስት እጅ አራቱን ደግሞ ለመሬታችሁ ዘር፣ እንዲሁም ለራሳችሁ፣ ለቤተ ሰቦቻችሁና ለልጆቻችሁ ምግብ ታደርጉታላችሁ።” እነርሱም፣ “እንግዲህ ሕይወታችንን አትርፈህልናል፤ በጌታችን ፊት ሞገስ ካገኘን፣ ለፈርዖን ገባሮች እንሆናለን” አሉት። ስለዚህ ዮሴፍ የምርቱ አንድ ዐምስተኛ ለፈርዖን እንዲገባ የሚያዝዝ የመሬት ሕግ በግብጽ አወጣ፤ ይህም ሕግ እስከ ዛሬ ይሠራበታል። በዚያ ጊዜ በፈርዖን እጅ ያልገባው መሬት የካህናቱ ብቻ ነበር። በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን በግብጽ አገር በጌሤም ይኖሩ ነበር፤ በዚያም ሀብት ንብረት ዐፈሩ፤ ቍጥራቸውም እጅግ እየበዛ ይሄድ ጀመር። ያዕቆብ በግብጽ ዐሥራ ሰባት ዓመት ኖረ፤ ዕድሜውም አንድ መቶ አርባ ሰባት ዓመት ነበር። እስራኤልም የሚሞትበት ጊዜ መቃረቡን እንደ ተረዳ ልጁን ዮሴፍን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “በአንተ ዘንድ ሞገስ ካገኘሁ እጅህን በጭኔ ላይ አኑረህ፣ በጎነትንና ታማኝነትን ልታደርግልኝ ቃል ግባልኝ፤ በምሞትበት ጊዜ በግብጽ አትቅበረኝ፤ እኔም ከአባቶቼ ጋራ ሳንቀላፋ፣ ከግብጽ አውጥተህ እነርሱ በተቀበሩበት ቦታ ቅበረኝ።” ዮሴፍም፣ “ዕሺ፣ እንዳልከኝ አደርጋለሁ” አለ። ያዕቆብም፣ “በል ማልልኝ” አለው። ዮሴፍም ማለለት፤ እስራኤልም በዐልጋው ራስጌ ላይ ሆኖ ጐንበስ አለ።
ዘፍጥረት 47 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 47
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 47:13-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች