የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፍጥረት 40:5-23

ዘፍጥረት 40:5-23 NASV

ታስረው የነበሩት የግብጽ የንጉሥ የመጠጥ አሳላፊዎች አለቃና የእንጀራ ቤቱ አዛዥ፣ በአንድ ሌሊት የየራሳቸውን ሕልም አዩ፤ የሁለቱም ሕልም ለየራሱ የተለየ ፍች ነበረው። በማግስቱም ጧት ዮሴፍ ወደ እነርሱ ሲገባ ተክዘው አገኛቸው። ስለዚህም፣ “ምነው ዛሬስ ፊታችሁ ላይ ሐዘን ይነበባል?” በማለት ዐብረውት በጌታው ግቢ የታሰሩትን የፈርዖን ሹማምት ጠየቃቸው። እነርሱም “ሁለታችንም ሕልም አየን፤ ነገር ግን የሚተረጕምልን ሰው አጣን” ሲሉ መለሱለት። ዮሴፍም፣ “ሁልጊዜስ ቢሆን የሕልም ትርጓሜ ከእግዚአብሔር የሚገኝ አይደለምን? እስኪ ያያችሁትን ሕልም ንገሩኝ” አላቸው። ስለዚህ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ እንዲህ ሲል ሕልሙን ለዮሴፍ ነገረው፤ “ከፊት ለፊቴ አንዲት የወይን ተክል አየሁ፤ ተክሏም ሦስት ሐረጎች ነበሯት፤ ወዲያው አቈጥቍጣ አበበች፤ ዘለላዎቿም ተንዠርግገው በሰሉ። የፈርዖንንም ጽዋ ይዤ ነበረ፤ የወይኑን ፍሬ ለቅሜ በጽዋው ውስጥ ጨምቄ ጽዋውን በእጁ ሰጠሁት።” ዮሴፍም እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ የሕልሙ ትርጓሜ ይህ ነው፤ ሦስቱ ሐረግ ሦስት ቀን ነው፤ በሦስት ቀን ውስጥ ፈርዖን ከእስር ቤት ያወጣሃል፣ ወደ ቀድሞ ሹመትህም ይመልስሃል፤ በፊት የመጠጥ አሳላፊ በነበርህበት ጊዜ ታደርግ እንደ ነበረው ሁሉ የፈርዖንን ጽዋ በእጁ ትሰጣለህ። እንግዲህ፣ በጎ ነገር በገጠመህ ጊዜ፣ እኔን ዐስበህ ቸርነት አድርግልኝ፤ ስለ እኔም ለፈርዖን ንገርልኝ፤ ከዚህም እስር ቤት አስወጣኝ፤ ከዕብራውያን ምድር ወደዚህ የመጣሁት በዐፈና ነው፤ አሁንም ቢሆን እዚህ እስር ቤት የተጣልሁት አንዳች ጥፋት ኖሮብኝ አይደለም።” የእንጀራ ቤት አዛዡም፣ ለመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ሕልም፣ የተሰጠው ፍች ደስ የሚያሰኝ መሆኑን ሲሰማ፣ የራሱን ሕልም ለዮሴፍ እንዲህ ሲል ነገረው፤ “እኔም ደግሞ ሕልም አይቻለሁ፤ ሦስት መሶቦች በራሴ ላይ ተሸክሜ ነበር፤ በላይኛው መሶብ ውስጥ ለፈርዖን የተዘጋጀ የተለያየ ምግብ ነበረበት፤ ወፎችም ራሴ ላይ ካለው መሶብ ይበሉ ነበር።” ዮሴፍም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “የሕልሙ ፍች ይህ ነው፤ ሦስቱ መሶብ ሦስት ቀን ነው፤ በሦስት ቀን ውስጥ ፈርዖን ከእስር ቤት ያወጣሃል፤ በዕንጨትም ላይ ይሰቅልሃል፤ ወፎችም ሥጋህን ይበሉታል።” በሦስተኛውም ቀን የፈርዖን የልደት በዓል ነበረ፤ ለሹማምቱም ሁሉ ግብር አበላ። በዚያ ዕለትም የመጠጥ አሳላፊዎችን አለቃና የእንጀራ ቤት አዛዡን ሹማምቱ ባሉበት ከእስር ቤት አወጣቸው። የመጠጥ አሳላፊዎቹን አለቃ ወደ ቀድሞ ሹመቱ መለሰው፤ እርሱም እንደ ቀድሞው ጽዋውን ለፈርዖን በእጁ ይሰጠው ጀመር። የእንጀራ ቤት አዛዡን ግን ልክ ዮሴፍ እንደ ተረጐመላቸው ሰቀለው። የሆነው ሆኖ፣ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ዮሴፍን አላስታወሰውም፤ ረሳው እንጂ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}