የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፍጥረት 4:1-16

ዘፍጥረት 4:1-16 NASV

አዳም ሚስቱን ሔዋንን ተገናኛት፤ እርሷም ፀንሳ ቃየንን ወለደች፤ “በእግዚአብሔር (ያህዌ) ርዳታ ወንድ ልጅ አገኘሁ” አለች። ደግሞም ወንድሙን አቤልን ወለደች። አቤል የበግ እረኛ፣ ቃየንም ዐራሽ ነበር። በአንድ ወቅት፣ ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት አቀረበ። አቤልም መጀመሪያ ከተወለዱት በጎች መካከል ስባቸውን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። እግዚአብሔር (ያህዌ) ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ በቃየንና በመሥዋዕቱ ግን አልተደሰተም፤ ስለዚህ ቃየን ክፉኛ ተናደደ፤ ፊቱም ጠቈረ። እግዚአብሔር አምላክም (ያህዌ ኤሎሂም) ቃየንን እንዲህ አለው፤ “ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቈረ? መልካም ብታደርግ ተቀባይነትን አታገኝምን? መልካም ባታደርግ ግን፣ ኀጢአት በደጅህ እያደባች ናት፤ ልታሸንፍህ ትፈልጋለች፤ አንተ ግን ተቈጣጠራት።” ቃየንም ወንድሙን አቤልን፣ “እስቲ ና፤ ወደ መስኩ እንውጣ” አለው፤ በመስኩም ሳሉ፣ ቃየን ወንድሙን አቤልን አጠቃው፤ ገደለውም። ከዚያም፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ቃየንን፣ “ወንድምህ አቤል የት ነው?” አለው። ቃየንም፣ “አላውቅም፤ እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን?” ሲል መለሰ። እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲህ አለ፤ “ምንድን ነው ያደረግኸው? የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል። እንግዲህ የተረገምህ ነህ፤ የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፏን ከከፈተችው መሬት ትሰደዳለህ። ብታርሳትም ፍሬዋን አትለግስህም፤ በምድር ላይ ኰብላይና ተንከራታች ትሆናለህ።” ቃየንም እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲህ አለው፤ “ቅጣቴ ልሸከመው ከምችለው በላይ ነው። እነሆ፤ ዛሬ ከምድሪቱ አባረርኸኝ፤ ከፊትህም እሸሸጋለሁ፤ በምድር ላይ ኰብላይና ተንከራታች እሆናለሁ፤ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል።” እግዚአብሔር (ያህዌ) ግን፣ “የለም! እንደርሱ አይሆንም፤ ማንም ቃየንን ቢገድል፣ ሰባት ዕጥፍ የበቀል ቅጣት ይቀበላል” አለው፤ ስለዚህ፣ ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው እግዚአብሔር (ያህዌ) በቃየን ላይ ምልክት አደረገለት። ቃየንም ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ወጥቶ ሄዶ፣ ከዔድን በስተ ምሥራቅ በምትገኝ ኖድ በተባለች ምድር ተቀመጠ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}