እያደርም የጌታው ሚስት ዐይኗን ጣለችበት፤ አፍ አውጥታም፣ “አብረኸኝ ተኛ” አለችው። እርሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፤ እንዲህም አላት፤ “ጌታዬ ያለውን ሁሉ በኀላፊነት ስለ ሰጠኝ፣ በቤቱ ውስጥ ስላለው ሁሉ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። በዚህ ቤት ላይ ከእኔ የበለጠ ኀላፊነት ያለው ማንም የለም፤ እርሱ ያልሰጠኝ ነገር ቢኖር፣ አንቺን ብቻ ነው፤ ያውም ሚስቱ ስለሆንሽ ነው፤ ታዲያ፣ እኔ ይህን ክፉ ድርጊት ፈጽሜ እንዴት በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፊት ኀጢአት እሠራለሁ?” ምንም እንኳ ዮሴፍን በየቀኑ ብትጐተጕተውም፣ አልሰማትም፤ ከእርሷ ጋር መተኛት ይቅርና አብሯትም መሆን አልፈቀደም። አንድ ቀን ዮሴፍ የዕለት ተግባሩን ለማከናወን ወደ ቤት ገባ፤ ከቤቱ አገልጋዮችም አንድም ሰው በቤት ውስጥ አልነበረም። እርሷም ልብሱን ጨምድዳ ይዛ “በል አብረኸኝ ተኛ” አለችው። እርሱ ግን ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ሸሽቶ ከቤት ወጣ። እርሷም ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ሸሽቶ መውጣቱን ባየች ጊዜ፣ የቤት አገልጋዮቿን ጠራች፤ እንዲህም አለቻቸው፤ “አያችሁ፤ ለካስ ይህ ዕብራዊ የመጣው መሣለቂያ ሊያደርገን ኖሯል! እዚህ ድረስ ሰተት ብሎ ገብቶ ካልተኛሁሽ አለኝ፤ እኔም ጩኸቴን ለቀቅሁት፤ ለርዳታ መጮኼን ሲሰማም፣ ልብሱን ከአጠገቤ ጥሎ ሸሽቶ ከቤት ወጣ።” ጌታውም ወደ ቤት እስኪመለስ ድረስ፣ ልብሱን አጠገቧ አቈየችው። ታሪኩንም እንዲህ ስትል ነገረችው፤ “አንተ ያመጣኸው ዕብራዊ ባሪያ መሣቂያ ሊያደርገን ወዳለሁበት ሰተት ብሎ ገባ፤ ታዲያ እኔ ድረሱልኝ ብዬ ስጮኽ ልብሱን አጠገቤ ጥሎ ሸሽቶ ወጣ።” ጌታውም፣ “ባሪያህ እንዲህ አደረገኝ” ብላ ሚስቱ የነገረችውን ታሪክ ሲሰማ ተቈጣ። ጌታውም ዮሴፍን ወስዶ፣ የንጉሥ እስረኞች ወደ ተጋዙበት እስር ቤት አስገባው።
ዘፍጥረት 39 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 39
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 39:7-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos