እግዚአብሔር ያዕቆብን፣ “ተነሥና ወደ ቤቴል ውጣ፤ እዚያም ተቀመጥ፤ ከወንድምህ ከዔሳው ሸሽተህ በሄድህ ጊዜ ለተገለጠልህ አምላክ በዚያ መሠዊያ ሥራ” አለው። ስለዚህም ያዕቆብ ለቤቱ ሰዎችና ዐብረውት ለነበሩት ሁሉ እንዲህ አላቸው፤ “በእናንተ ዘንድ ያሉትን ባዕዳን አማልክት አስወግዱ፤ ሰውነታችሁን አንጹ፤ ልብሳችሁንም ለውጡ። ተነሥተን ወደ ቤቴል እንውጣ፤ እዚያም በመከራዬ ጊዜ ለሰማኝ፣ በሄድሁበትም ስፍራ ሁሉ ላልተለየኝ አምላክ መሠዊያ እሠራለሁ።” ስለዚህ በእነርሱ ዘንድ የነበሩትን ባዕዳን አማልክት ሰብስበው፣ የጆሮ ጕትቾቻቸውን አውልቀው ለያዕቆብ ሰጡት። ያዕቆብም ወስዶ ሴኬም አጠገብ ካለው ወርካ ዛፍ ሥር ቀበራቸው። ያንም ቦታ ለቅቀው ሄዱ፤ እግዚአብሔርም በዙሪያቸው በነበሩት ከተሞች ሁሉ ላይ ፍርሀትና ድንጋጤ ስለ ለቀቀባቸው የያዕቆብን ልጆች ያሳደዳቸው አልነበረም። ያዕቆብና ዐብረውት የነበሩት ሰዎች ሁሉ፣ በከነዓን ወደምትገኘው፣ ቤቴል ወደተባለችው ወደ ሎዛ ደረሱ። ያዕቆብም በዚያ ስፍራ መሠዊያ ሠርቶ፣ ስሙን ኤል-ቤቴል አለው፤ ምክንያቱም ከወንድሙ ሸሽቶ በሄደ ጊዜ እግዚአብሔር የተገለጠለት በዚህ ቦታ ነበር። በዚህ ጊዜ የርብቃ ሞግዚት ዲቦራ ሞተች፤ ከቤቴል ዝቅ ብሎ በሚገኘው ወርካ ዛፍ ሥር ተቀበረች። ከዚህ የተነሣም ያ ቦታ አሎንባኩት ተባለ። ያዕቆብ ከሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ከተመለሰ በኋላ፣ እግዚአብሔር ለያዕቆብ ዳግመኛ ተገለጠለት፤ ባረከውም። እግዚአብሔርም፣ “እስካሁን ስምህ ያዕቆብ ነበረ፤ ከእንግዲህ ያዕቆብ ተብለህ አትጠራም፤ ነገር ግን ስምህ እስራኤል ይባላል” አለው። ስለዚህም እስራኤል ብሎ ጠራው። ደግሞም እግዚአብሔር ያዕቆብን እንዲህ አለው፤ “እኔ ሁሉን ቻይ አምላክ ነኝ፤ ብዛ ተባዛ፤ ሕዝብና የሕዝቦች ማኅበር ከአንተ ይወጣሉ፤ ነገሥታትም ከአብራክህ ይከፈላሉ። ለአብርሃምና ለይሥሐቅ የሰጠኋትን ምድር ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ከአንተም በኋላ ይህችኑ ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ።” እግዚአብሔርም ከርሱ ጋራ ከተነጋገረበት ስፍራ ወደ ላይ ወጣ። ያዕቆብም እግዚአብሔር ከርሱ ጋራ በተነጋገረበት ስፍራ የድንጋይ ሐውልት አቆመ፤ በሐውልቱ ላይ የመጠጥ ቍርባን አፈሰሰ፤ ዘይትም አፈሰሰበት። ያዕቆብም፣ እግዚአብሔር ከርሱ ጋራ የተነጋገረበትን ስፍራ ቤቴል ብሎ ጠራው።
ዘፍጥረት 35 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 35
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 35:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች