ራሔል ለያዕቆብ አንድም ልጅ እንዳልወለደችለት ባየች ጊዜ በእኅቷ ቀናች። ስለዚህ ያዕቆብን፣ “ልጅ ስጠኝ፤ አለዚያ እሞታለሁ” አለችው። ያዕቆብም ራሔልን ተቈጥቶ “እኔ እንዳትወልጂ ያደረገሽን እግዚአብሔርን መሰልኹሽን?” አላት። እርሷም፣ “እነሆ፤ አገልጋዬ ባላ አለችልህ፤ ልጆች እንድትወልድልኝና እኔም ደግሞ በርሷ አማካይነት ልጆች እንዳገኝ ከርሷ ጋራ ተኛ” አለችው። ስለዚህም አገልጋይዋን ባላን ሚስት እንድትሆነው ሰጠችው፤ ያዕቆብም ዐብሯት ተኛ፤ እርሷም ፀነሰች፤ ለያዕቆብም ወንድ ልጅ ወለደችለት። ራሔልም፣ “እግዚአብሔር ፈርዶልኛል፣ ልመናዬንም ሰምቶ ወንድ ልጅ ሰጥቶኛል” አለች። ስለዚህ ስሙን ዳን ብላ አወጣችለት። የራሔል አገልጋይ ባላ እንደ ገና ፀነሰች፤ ለያዕቆብም ሁለተኛ ወንድ ልጅ ወለደች። ራሔልም፣ “እኅቴን ብርቱ ትግል ገጥሜ አሸነፍሁ” አለች፤ ስሙንም ንፍታሌም ብላ አወጣችለት። ልያም ልጅ መውለድ ማቆሟን እንደ ተረዳች፣ አገልጋይዋን ዘለፋን ሚስት እንድትሆነው ለያዕቆብ ሰጠችው። የልያ አገልጋይ ዘለፋም ለያዕቆብ ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ልያም፣ “ምን ዐይነት መታደል ነው” አለች፤ ስሙንም ጋድ ብላ አወጣችለት። የልያም አገልጋይ ዘለፋ፤ ለያዕቆብ ሁለተኛ ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ልያም፣ “ምንኛ ደስተኛ ሆንሁ ከእንግዲህ ሴቶች ደስተኛዋ ይሉኛል” አለች፤ ስሙንም አሴር ብላ አወጣችለት። ስንዴ በሚታጨድበት ወቅት፣ ሮቤል ወደ ሜዳ ወጣ፤ እንኮይም አግኝቶ ለእናቱ ለልያ አመጣላት። ራሔልም ልያን፣ “እባክሽን ልጅሽ ካመጣልሽ እንኮይ ስጪኝ” አለቻት። ልያም፣ “ባሌን የቀማሽኝ አነሰና የልጄን እንኮይ ደግሞ ልትወስጂ አማረሽ?” አለቻት። ራሔልም፣ “ስለ ልጅሽ እንኮይ ዛሬ ከአንቺ ጋራ ይደር” አለቻት። በዚያች ምሽት ያዕቆብ ከዕርሻ ሲመለስ፣ ልያ ወጥታ ተቀበለችውና፣ “በልጄ እንኮይ ስለ ተከራየሁህ የዛሬው ዐዳርህ ከእኔ ጋራ ነው” አለችው፤ ያዕቆብም በዚያች ሌሊት ከርሷ ጋራ ዐደረ። እግዚአብሔር የልያን ጸሎት ሰማ፤ ፀነሰች፤ ለያዕቆብም ዐምስተኛውን ወንድ ልጅ ወለደች። ልያም፣ “አገልጋዬን ለባሌ በመስጠቴ እግዚአብሔር ክሶኛል” አለች፤ ስሙንም ይሳኮር ብላ አወጣችለት። ልያ አሁንም ደግማ ፀነሰች፤ ለያዕቆብም ስድስተኛውን ወንድ ልጅ ወለደች። እርሷም፣ “እግዚአብሔር በከበረ ስጦታ ዐድሎኛል፣ ስድስት ወንዶች ልጆች ስለ ወለድሁለት፣ ከእንግዲህ ባሌ አክብሮ ይይዘኛል”። አለች፤ ስሙንም ዛብሎን አለችው። ከዚያም በኋላ ሴት ልጅ ወለደች፤ ስሟንም ዲና አለቻት። እግዚአብሔርም ራሔልን ዐሰባት፤ ልመናዋንም ሰምቶ ማሕፀኗን ከፈተላት። ከዚያም ፀንሳ፣ ወንድ ልጅ ወለደችና “እግዚአብሔር ዕፍረቴን አስወገደልኝ” አለች፤ ስሙንም፣ “እግዚአብሔር ሌላ ወንድ ልጅ ጨምሮ ይስጠኝ” ስትል፣ ዮሴፍ አለችው። ራሔል ዮሴፍን ከወለደች በኋላ ያዕቆብ ላባን እንዲህ አለው፤ “ወደ ገዛ ቤቴ፣ ወደ አገሬ እንድመለስ አሰናብተኝ፤ የድካሜ ዋጋ የሆኑትን ሚስቶቼንና ልጆቼን ስጠኝና ይዣቸው ልሂድ፤ መቼም የቱን ያህል እንዳገለገልሁህ ታውቃለህ” አለው። ላባም እንዲህ አለው፤ “በጎ ፈቃድህ ቢሆን፣ እባክህ እዚሁ ከእኔ ጋራ ተቀመጥ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔርም በአንተ ምክንያት እንደ ባረከኝ በንግርት ተረድቻለሁ፤ ይልቅስ ይገባኛል የምትለውን ደመወዝ ንገረኝና እከፍልሃለሁ።” ያዕቆብም እንዲህ አለው፤ “መቼም እንዴት እንዳገለገልሁህ፣ ከብቶችህ በእኔ ጥበቃ ምን ያህል እንደ ተመቻቸው አንተ ታውቃለህ። እኔ ከመምጣቴ በፊት ጥቂት የነበረው ሀብትህ ዛሬ ተትረፍርፏል፣ በተሰማራሁበት ሁሉ እግዚአብሔር በረከቱን አብዝቶልሃል። ታዲያ፣ ስለ ራሴ ቤት የማስበው መቼ ነው?” ላባም፣ “ታዲያ ምን ልስጥህ?” ሲል ጠየቀው። ያዕቆብም መልሶ እንዲህ አለው፤ “ምንም አትስጠኝ፤ ነገር ግን የምጠይቅህን አንዲት ነገር ብቻ ብታደርግልኝ ከብቶችህን ማገዴን እቀጥላለሁ፤ በመንጎቹ መካከል ዛሬ ልዘዋወርና ከበጎቹ መካከል ዝንጕርጕር የሆኑትን፣ ነቍጣ ያለባቸውንና ጥቋቍሮቹን እንዲሁም ከፍየሎቹ ነቍጣ ያለባቸውንና ዝንጕርጕሮቹን ልምረጥ፤ እነዚህ ደመወዜ ይሁኑ። ወደ ፊት ደመወዜን ለመቈጣጠር በምትመጣበት ጊዜ ታማኝነቴ ይታወቃል፤ በመንጎቼ መካከል ዝንጕርጕር ወይም ነቍጣ የሌለበት ፍየል ወይም ጥቍር ያልሆነ በግ ቢገኝ ያ እንደ ተሰረቀ ይቈጠር።” ላባም፣ “ዕሺ፣ ይሁን፤ ባልኸው ተስማምቻለሁ” አለው። ነገር ግን በዚያ ዕለት ከተባዕት ፍየሎች ሽመልመሌ የሆኑትን ወይም ነቍጣ ያለባቸውን ሁሉ፣ እንዲሁም ከእንስት ፍየሎች ነቍጣ ያለባቸውን ዝንጕርጕር የሆኑትን ሁሉ፣ ማንኛውንም ነጭ ያለበትን ሁሉ መረጠ፤ ደግሞም ጥቋቍር የሆኑትንም በጎች ሁሉ ለየና ወንዶች ልጆቹን አስጠበቃቸው። ከዚያም በርሱና በያዕቆብ መካከል የሦስት ቀን መንገድ ርቀት እንዲኖር አደረገ፤ ያዕቆብም የቀሩትን የላባን መንጎች ማገዱን ቀጠለ። ነገር ግን ያዕቆብ ርጥብ የልብን፣ የለውዝና የኤርሞን በትሮች ወሰደ፤ ቅርፊታቸውንም በቀጭን ልጦ እያነሣ የበትሮቹ ግንድ ነጩ እንዲታይ፣ ሽመልመሌ መልክ እንዲኖራቸው አደረገ። የላጣቸውንም በትሮች መንጎቹ ውሃ ለመጠጣት ሲመጡ ከፊት ለፊት እንዲያዩአቸው በማጠጫ ገንዳዎቹ ሁሉ አስቀመጠ። መንጎቹም ስሜታቸው ሲነሣሣና ውሃ ለመጠጣት ሲመጡ፣ በትሮቹን ፊት ለፊት እያዩ ይሳረሩ ነበር፤ ሽመልመሌ፣ ዝንጕርጕርና ነቍጣ የጣለባቸውንም ግልገሎች ወለዱ። ያዕቆብ ግልገሎቹን ለብቻ ለያቸው፤ የቀሩትንም የላባ መንጎች ሽመልመሌና ጥቋቍር በሆኑት በጎች ትይዩ አቆማቸው፤ በዚህም መሠረት የራሱ መንጋ ከላባ መንጋ ጋራ እንዳይቀላቀል ለብቻ ለየ። ያዕቆብም ብርቱ እንስቶች አውራ ፈልገው በሚቅበጠበጡበት ጊዜ፣ በትሮቹ አቅራቢያ እንዲጠቁ በትሮቹን በውሃ ገንዳዎቹ ውስጥ ፊት ለፊታቸው ያስቀምጥ ነበር፤ ደካማ በሆኑት እንስቶች ፊት ግን፣ በትሮቹን አያስቀምጥም ነበር፤ ስለዚህ ደካማ ደካማዎቹ ለላባ ሲሆኑ፣ ብርቱ ብርቱዎቹ ለያዕቆብ ሆኑ። በዚህም ሁኔታ ይህ ሰው እጅግ ባለጠጋ ሆነ፤ የብዙ መንጎች፣ የሴትና የወንድ አገልጋዮች፣ እንዲሁም የግመሎችና የአህዮች ባለቤት ሆነ።
ዘፍጥረት 30 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 30
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 30:1-43
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos