ቀድሞ በአብርሃም ዘመን ከደረሰው ራብ ሌላ፣ በአገሩ ላይ ራብ ሆነ። ይሥሐቅም የፍልስጥኤም ንጉሥ አቢሜሌክ ወደሚኖርበት ወደ ጌራራ ሄደ። በዚያም እግዚአብሔር ለይሥሐቅ ተገልጦ እንዲህ አለው፤ “እኔ በምነግርህ ምድር ተቀመጥ እንጂ፣ ወደ ግብጽ አትውረድ፤ ለጥቂት ጊዜ እዚሁ አገር ተቀመጥ፤ እኔም ካንተ ጋራ እሆናለሁ፤ እባርክሃለሁም፤ ይህን ምድር በሙሉ ለአንተና ለዘርህ በመስጠት ለአባትህ ለአብርሃም በመሐላ የገባሁለትን ቃል አጸናለሁ። ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፤ ይህን ምድር በሙሉ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ የምድር ሕዝቦችም ሁሉ በዘርህ አማካይነት ይባረካሉ። ይኸውም አብርሃም ቃሌን ሰምቶ፣ ድንጋጌዬን፣ ትእዛዜን፣ ሥርዐቴንና ሕጌን በመጠበቁ ነው።” ስለዚህ ይሥሐቅ በጌራራ ተቀመጠ። የዚያም አገር ሰዎች ስለ ሚስቱ በጠየቁት ጊዜ፣ “እኅቴ ናት” አለ፤ ምክንያቱም፣ “ሚስቴ ናት ብል ርብቃ ቈንጆ ስለ ሆነች፣ ያገሬው ሰዎች በርሷ ምክንያት ይገድሉኛል” በማለት ፈርቶ ነበር። ይሥሐቅ ብዙ ጊዜ በዚያ ከኖረ በኋላ፣ የፍልስጥኤም ንጉሥ አቢሜሌክ አንድ ቀን ወደ ውጭ ሲመለከት፣ ይሥሐቅ ሚስቱን ርብቃን ሲዳራት አየ። አቢሜሌክም ይሥሐቅን ጠርቶ፣ “እርሷ ሚስትህ ሆና ሳለች፣ እንዴት ‘እኅቴ ናት’ ትላለህ?” አለው። ይሥሐቅም፣ “በርሷ ሰበብ፣ ሕይወቴን እንዳላጣ ብዬ ነው” አለው። አቢሜሌክም መልሶ፣ “እንዲህ ያለ ነገር ያደረግህብን ለምንድን ነው? ከሰዎቻችን አንዱ ሚስትህን ቢደፍራት ኖሮ በእኛ ላይ በደል አስከትለህብን ነበር እኮ!” አለው። አቢሜሌክም፣ “ይህን ሰው ወይም ሚስቱን የነካ በሞት ይቀጣል” የሚል ትእዛዝ ለሕዝቡ ሁሉ አወጣ። ይሥሐቅም በዚያች ምድር ዘር ዘራ፣ እግዚአብሔርም ባረከለትና በዚያ ዓመት መቶ ዕጥፍ አመረተ። ሰውየውም እጅግ ባለጠጋ እስኪሆን ድረስ ሀብት በሀብት ላይ እየተጨመረለት ሄደ። ብዙ የበግና የፍየል መንጋ፣ ብዙ ከብት፣ ብዙ አገልጋዮችም ስለ ነበሩት፣ ፍልስጥኤማውያን ተመቀኙት። ከዚህ የተነሣ ፍልስጥኤማውያን፣ አባቱ አብርሃም በሕይወት በነበረበት ጊዜ፣ የአብርሃም አገልጋዮች የቈፈሯቸውን የውሃ ጕድጓዶች በሙሉ ዐፈር ሞልተው ደፈኗቸው። አቢሜሌክም ይሥሐቅን፣ “ከእኛ ይልቅ ኀያል ሆነሃልና አገራችንን ልቀቅልን” አለው። ይሥሐቅም ያን ቦታ ትቶ ሄደ፤ በጌራራ ሸለቆም ተቀመጠ። ይሥሐቅም በአባቱ በአብርሃም ጊዜ ተቈፍረው የነበሩትን፣ አባቱ ከሞተ በኋላ ፍልስጥኤማውያን የደፈኗቸውን የውሃ ጕድጓዶች እንደ ገና እንዲከፈቱ አደረገ፤ አባቱ ቀድሞ ባወጣላቸው ስምም መልሶ ጠራቸው። የይሥሐቅ አገልጋዮች በሸለቆው ውስጥ ሲቈፍሩ፣ ከጕድጓዱ የሚፈልቅ ውሃ አገኙ። የጌራራ እረኞች ግን፣ “ውሃው የእኛ ነው” በማለት ከይሥሐቅ እረኞች ጋራ ጠብ አነሡ፤ ከዚህ የተነሣ ይሥሐቅ ያን የውሃ ጕድጓድ ኤሴቅ ብሎ ጠራው፤ በጕድጓዱ ምክንያት ተጣልተውታልና። አሁንም እንደ ገና ሌላ የውሃ ጕድጓድ ቈፈሩ፤ አሁንም ሌላ ግጭት ተፈጠረ፤ ስለዚህ የውሃ ጕድጓዱን ስጥና ብሎ ጠራው። ይሥሐቅም ያን ቦታ ትቶ ሌላ ስፍራ ላይ የውሃ ጕድጓድ አስቈፈረ፤ በዚህ ጊዜ ግን አንድም ሰው ጠብ አላነሣበትም፤ ስለዚህ ያን የውሃ ጕድጓድ፣ “አሁን እግዚአብሔር ሰፊ ቦታ ሰጥቶናል፤ እኛም በምድር ላይ እንበዛለን” ሲል ርኆቦት ብሎ ጠራው። ከዚያም ይሥሐቅ ወደ ቤርሳቤህ ወጣ። በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር ተገለጠለትና፣ “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ፤ ከአንተ ጋራ ነኝና አትፍራ፤ እባርክሃለሁ፤ ስለ አገልጋዬም ስለ አብርሃም ስል ዘርህን አበዛለሁ” አለው። ይሥሐቅም በዚያ ስፍራ መሠዊያ ሠርቶ፣ የእግዚአብሔርን ስም ጠራ፤ ድንኳንም ተከለ፤ አገልጋዮቹም በዚያ የውሃ ጕድጓድ ቈፈሩ። አቢሜሌክም ከአማካሪው ከአዘኮትና ከሰራዊቱ አዛዥ ከፊኮል ጋራ ከጌራራ ተነሥቶ ይሥሐቅ ወዳለበት ስፍራ መጣ። ይሥሐቅም፣ “ጠልታችሁኝ ካባረራችሁኝ በኋላ፣ አሁን ደግሞ ለምን መጣችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ መሆኑን በግልጽ ተረድተናል፤ ስለዚህም፣ ‘በመሐላ የጸና ውል በመካከላችን መኖር አለበት’ አልን፤ ይህም በእኛና በአንተ መካከል የሚጸና ውል ነው፤ አሁንም ከአንተ ጋራ ስምምነት እናድርግ፤ አንተን እንዳልጐዳንህ፣ ነገር ግን በጎነትን እንዳሳየንህና በሰላም እንደ ሸኘንህ ሁሉ፣ አንተም ክፉ እንዳታደርግብን በመካከላችን ውል ይደረግ፤ አንተን እንደሆን መቼም እግዚአብሔር ባርኮሃል።” ይሥሐቅም ድግስ ደግሶ አበላቸው፤ አጠጣቸው። በማግስቱም በማለዳ ተነሥተው፣ በመካከላቸው መሐላ ፈጸሙ። ይሥሐቅም አሰናበታቸው፤ እነርሱም በሰላም ሄዱ። በዚያ ዕለት፣ የይሥሐቅ አገልጋዮች መጥተው ስለ ቈፈሩት የውሃ ጕድጓድ ነገሩት፤ “ውሃ እኮ አገኘን!” አሉት። እርሱም የውሃውን ጕድጓድ ሳቤህ አለው፤ ከዚያም የተነሣ የከተማዪቱ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ቤርሳቤህ ተብሎ ይጠራል።
ዘፍጥረት 26 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 26
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 26:1-33
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
YouVersion የእርስዎን ተሞክሮ ግላዊ ለማድረግ ኩኪዎችን ይጠቀማል። የእኛን ድረ ገጽ በመጠቀም፣ በግለሰብነት መመሪያችን ላይ እንደተገለጸው የእኛን የኩኪዎች አጠቃቀም ተቀብለዋል
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች