እግዚአብሔር በተናገረው መሠረት ሣራን ዐሰባት፤ የገባውንም ተስፋ ፈጸመላት። ሣራ ፀነሰች፤ ልክ እግዚአብሔር ባለው ጊዜ ለአብርሃም ወንድ ልጅ ወለደችለት። አብርሃም፣ ሣራ የወለደችለትን ልጅ ስሙን ይሥሐቅ አለው። አብርሃም፣ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ልጁን ይሥሐቅን በተወለደ በስምንተኛው ቀን ገረዘው። አብርሃም፣ ልጁ ይሥሐቅ ሲወለድለት፣ ዕድሜው መቶ ዓመት ነበረ። ሣራም፣ “እግዚአብሔር ሣቅ አድሎኛል፤ ስለዚህ፣ ይህን የሚሰማ ሁሉ ከእኔ ጋራ ይሥቃል” አለች። ደግሞም፣ “ለመሆኑ፣ ‘ሣራ ልጆች ታጠባለች’ ብሎ ለአብርሃም ማን ተናግሮት ያውቅ ነበር? ይኸው በስተርጅናው ወንድ ልጅ ወለድሁለት” አለች። ሕፃኑ አደገ፤ ጡት መጥባቱንም ተወ። አብርሃምም ይሥሐቅ ጡት በጣለባት ዕለት ታላቅ ድግስ ደገሰ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ግብጻዊቷ አጋር ለአብርሃም የወለደችለት እስማኤል በይሥሐቅ ላይ ሲያሾፍበት ሣራ አየች፤ አብርሃምንም፣ “ይህችን ባሪያ ከነልጇ አባርራት፤ የዚህች ባሪያ ልጅ፣ ከልጄ ከይሥሐቅ ጋራ አይወርስምና” አለችው። እስማኤል ልጁ ስለ ሆነ ነገሩ አብርሃምን እጅግ አስጨነቀው። እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ስለ ልጁም ሆነ ስለ አገልጋይህ ሐሳብ አይግባህ፤ ዘር የሚጠራልህ በይሥሐቅ በኩል ስለ ሆነ፣ ሣራ የምትልህን ሁሉ ስማ። የአገልጋይህም ልጅ የራስህ ልጅ ስለ ሆነ፣ እርሱንም ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁ።” በማግስቱም አብርሃም ማልዶ ተነሣ። ጥቂት ምግብ ወስዶ፣ ውሃ በእርኮት አድርጎ ለአጋር ሰጣት፤ በትከሻዋም አሸክሟት ከነልጇ አሰናበታት። እርሷም ሄደች፤ በቤርሳቤህም ምድረ በዳ ትንከራተት ጀመር። በእርኮት የነበረው ውሃ ባለቀ ጊዜ፣ ልጁን ከአንድ ቍጥቋጦ ሥር አስቀመጠችው። ከዚያም፣ “ልጁ ሲሞት ዐይኔ አያይም” ብላ፣ የቀስት ውርወራ ያህል ርቃ ዐረፍ አለች፤ እርሷም እየተንሰቀሰቀች ታለቅስ ጀመር። እግዚአብሔርም የልጁን ጩኸት ሰማ። የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ አላት፤ “አጋር ሆይ፤ ምን ሆነሻል? ልጅሽ ከተኛበት ሲያለቅስ እግዚአብሔር ሰምቶታል፤ ስለዚህ አትፍሪ። ተነሥተሽ ልጁን አንሺው፤ ያዢውም፤ ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና።” እግዚአብሔርም ዐይኖቿን ከፈተላት፤ የውሃ ጕድጓድም አየች፤ ሄዳም በእርኮቱ ውሃ ሞልታ ልጇን አጠጣች። እግዚአብሔር ከልጁ ጋራ ነበር፤ ልጁም እያደገ ሄደ፤ መኖሪያውንም በምድረ በዳ ውስጥ አደረገ፤ ጐበዝ ቀስተኛም ሆነ። በፋራን ምድረ በዳ ሳለም፣ እናቱ ከግብጽ አንዲት ሴት አምጥታ አጋባችው። በዚያ ጊዜ አቢሜሌክ ከሰራዊቱ አለቃ ከፊኮል ጋራ ሆኖ አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “በምታደርገው ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ነው። እንግዲህ እኔንና ልጆቼን፣ ዘሬንም በመሸንገል አንዳች ክፉ ነገር እንዳታደርስብን በእግዚአብሔር ፊት ማልልኝ። እኔ ለአንተ ቸርነት እንዳደረግሁ፣ አንተም ለእኔና በእንግድነት ለተቀመጥህባት ለዚህች ምድር ቸርነት አድርግ።” አብርሃምም፣ “ዕሺ፤ እምላለሁ” አለ። ከዚያም አብርሃም፣ የአቢሜሌክ አገልጋዮች ነጥቀው ስለያዙበት የውሃ ጕድጓድ መከፋቱን ለአቢሜሌክ ገለጠለት። አቢሜሌክም፣ “መቼም ይህን ድርጊት ማን እንደ ፈጸመ በበኩሌ አላውቅም፤ አንተም አልነገርኸኝም፤ ነገሩንም ገና አሁን መስማቴ ነው” አለው። ስለዚህ አብርሃም፣ በጎችና ከብቶች አምጥቶ ለአቢሜሌክ ሰጠው፤ ሁለቱም በመካከላቸው የስምምነት ውል አደረጉ። አብርሃም ከመንጋው ሰባት እንስት በጎች ለየ፤ አቢሜሌክም፣ “እነዚህን ሰባት እንስት በጎች ለይተህ ለብቻ ያቆምሃቸው ለምንድን ነው?” ሲል አብርሃምን ጠየቀው። አብርሃምም፣ “ይህን የውሃ ጕድጓድ የቈፈርሁ እኔ ለመሆኔ ምስክር እንዲሆን እነዚህን ሰባት እንስት በጎች ዕንካ ተቀበለኝ” አለው። ስለዚህ ቦታው፣ ሁለቱ ተማምለው የተስማሙበት ስፍራ በመሆኑ ቤርሳቤህ ተባለ። በቤርሳቤህ የስምምነት ውል ካደረጉ በኋላ፣ አቢሜሌክና የሰራዊቱ አለቃ ፊኮል ወደ ፍልስጥኤማውያን ምድር ተመለሱ። አብርሃምም በቤርሳቤህ የተምር ዛፍ ተከለ፤ በዚያም እግዚአብሔር የዘላለም አምላክን ስም ጠራ። አብርሃምም በፍልስጥኤማውያን ምድር ለረዥም ጊዜ በእንግድነት ኖረ።
ዘፍጥረት 21 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 21
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 21:1-34
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች