እግዚአብሔር (ያህዌ) በተናገረው መሠረት ሣራን ዐሰባት፤ የገባውንም ተስፋ ፈጸመላት። ሣራ ፀነሰች፤ ልክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ባለው ጊዜ ለአብርሃም ወንድ ልጅ ወለደችለት። አብርሃም፣ ሣራ የወለደችለትን ልጅ ስሙን ይስሐቅ አለው። አብርሃም፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ባዘዘው መሠረት ልጁን ይስሐቅን በተወለደ በስምንተኛው ቀን ገረዘው። አብርሃም፣ ልጁ ይስሐቅ ሲወለድለት፣ ዕድሜው መቶ ዓመት ነበረ። ሣራም፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሣቅ አድሎኛል፤ ስለዚህ፣ ይህን የሚሰማ ሁሉ ከእኔ ጋር ይሥቃል” አለች። ደግሞም፣ “ለመሆኑ፣ ‘ሣራ ልጆች ታጠባለች’ ብሎ ለአብርሃም ማን ተናግሮት ያውቅ ነበር? ይኸው በስተርጅናው ወንድ ልጅ ወለድሁለት” አለች። ሕፃኑ አደገ፤ ጡት መጥባቱንም ተወ። አብርሃምም ይስሐቅ ጡት በጣለባት ዕለት ታላቅ ድግስ ደገሰ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ግብፃዊቷ አጋር ለአብርሃም የወለደችለት እስማኤል በይስሐቅ ላይ ሲያሾፍበት ሣራ አየች፤ አብርሃምንም፣ “ይህችን ባሪያ ከነልጇ አባርልኝ፤ ምንም ቢሆን የዚህች ባሪያ ልጅ፣ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር ውርስ አይካፈልም አለች።” እስማኤል ልጁ ስለሆነ ነገሩ አብርሃምን እጅግ አስጨነቀው። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ስለ ልጁም ሆነ ስለ አገልጋይህ ሐሳብ አይግባህ፤ ዘር የሚጠራልህ በይስሐቅ በኩል ስለሆነ፣ ሣራ የምትልህን ሁሉ ስማ። የአገልጋይህም ልጅ የራስህ ልጅ ስለሆነ፣ እርሱንም ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁ።” በማግስቱም አብርሃም ማልዶ ተነሣ። ጥቂት ምግብ ወስዶ፣ ውሃ በእርኮት አድርጎ ለአጋር ሰጣት፤ በትከሻዋም አሸክሟት ከነልጇ አሰናበታት። እርሷም ሄደች፤ በቤርሳቤህም ምድረ በዳ ትንከራተት ጀመር። በእርኮት የነበረው ውሃ ባለቀ ጊዜ፣ ልጁን ከአንድ ቍጥቋጦ ሥር አስቀመጠችው። ከዚያም፣ “ልጁ ሲሞት ዐይኔ አያይም” ብላ፣ የቀስት ውርወራ ያህል ርቃ ዐረፍ አለች፤ እርሷም እየተንሰቀሰቀች ታለቅስ ጀመር። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) የልጁን ጩኸት ሰማ። የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ አላት፤ “አጋር ሆይ፤ ምን ሆነሻል? ልጅሽ ከተኛበት ሲያለቅስ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰምቶታል፤ ስለዚህ አትፍሪ። ተነሥተሽ ልጁን አንሺው፤ ያዢውም፤ ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና።” እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ዐይኖቿን ከፈተላት፤ የውሃ ጕድጓድም አየች፤ ሄዳም በእርኮቱ ውሃ ሞልታ ልጇን አጠጣች። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከልጁ ጋር ነበር፤ ልጁም እያደገ ሄደ፤ መኖሪያውንም በምድረ በዳ ውስጥ አደረገ፤ ጐበዝ ቀስተኛም ሆነ። በፋራን ምድረ በዳ ሳለም፣ እናቱ ከግብፅ አንዲት ሴት አምጥታ አጋባችው።
ዘፍጥረት 21 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 21
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 21:1-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos