የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፍጥረት 2:7-25

ዘፍጥረት 2:7-25 NASV

እግዚአብሔር አምላክ ከምድር ዐፈር ወስዶ ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ። እግዚአብሔር አምላክ በምሥራቅ፣ በዔድን የአትክልት ስፍራ አዘጋጀ፤ ያበጀውንም ሰው በዚያ አኖረው። እግዚአብሔር አምላክም ለዐይን የሚያስደስት ለመብልም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር አበቀለ፤ በአትክልቱ ቦታ መካከልም የሕይወት ዛፍ ነበረ፤ እንዲሁም መልካምና ክፉን መለየት የሚያስችለው የዕውቀት ዛፍ ነበረ። የአትክልት ስፍራውን የሚያጠጣ ወንዝ ከዔድን ይፈስስ ነበር፤ ከዚያም በአራት ተከፍሎ ይወጣ ነበር። የመጀመሪያው፣ ወርቅ በሚገኝበት በኤውላጥ ምድር ዙሪያ ሁሉ የሚፈስሰው የፊሶን ወንዝ ነው። ኤውላጥ ምርጥ የሆነ ወርቅ፣ መልካም መዐዛ ያለው ከርቤና የከበረ ድንጋይ የሚገኙበት ምድር ነው። ሁለተኛው፣ በኢትዮጵያ ምድር ዙሪያ ሁሉ የሚፈስሰው የግዮን ወንዝ ነው። ሦስተኛው፣ ከአሦር በስተምሥራቅ የሚፈስሰው የጤግሮስ ወንዝ ሲሆን፣ አራተኛው የኤፍራጥስ ወንዝ ነው። እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ወስዶ እንዲያለማትና እየተንከባከበ እንዲጠብቃት በዔድን የአትክልት ስፍራ አስቀመጠው። እግዚአብሔር አምላክ ሰውን እንዲህ በማለት አዘዘው፤ “በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ትበላለህ። ነገር ግን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከርሱ በበላህ ቀን በርግጥ ትሞታለህ።” ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ፣ “ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለምና የሚስማማውን ረዳት አበጅለታለሁ” አለ። እግዚአብሔር አምላክ የዱር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ከምድር ሠርቶ ነበር፤ ለእያንዳንዳቸውም ምን ስም እንደሚያወጣላቸው ለማየት ወደ አዳም አመጣቸው። አዳም ሕይወት ላላቸው ፍጥረታት ሁሉ ያወጣላቸው ስም መጠሪያቸው ሆነ። ስለዚህ አዳም ለከብቶች፣ ለሰማይ ወፎች፣ ለዱር አራዊት ሁሉ ስም አወጣላቸው። ይሁን እንጂ ለአዳም ተስማሚ ረዳት አልተገኘለትም ነበር። እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ላይ ከባድ እንቅልፍ ጣለበት፤ አንቀላፍቶም ሳለ ከጐድኑ አንዲት ዐጥንት ወስዶ፣ ስፍራውን በሥጋ ሞላው። እግዚአብሔር አምላክ ከአዳም የወሰዳትን ዐጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት። አዳምም እንዲህ አለ፤ “እነሆ፤ ይህች ዐጥንት ከዐጥንቴ፣ ሥጋም ከሥጋዬ ናት። ከወንድ ተገኝታለችና ‘ሴት’ ትባል።” ስለዚህ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ ከሚስቱ ጋራ ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። አዳምና ሚስቱ፣ ሁለቱም ዕራቍታቸውን ነበሩ፤ ይሁን እንጂ አይተፋፈሩም ነበር።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}