እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ወስዶ እንዲያለማትና እየተንከባከበ እንዲጠብቃት በዔድን የአትክልት ስፍራ አስቀመጠው። እግዚአብሔር አምላክ ሰውን እንዲህ በማለት አዘዘው፤ “በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ትበላለህ። ነገር ግን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከርሱ በበላህ ቀን በርግጥ ትሞታለህ።” ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ፣ “ሰው ብቻውን መሆኑ መልካም አይደለምና የሚስማማውን ረዳት አበጅለታለሁ” አለ። እግዚአብሔር አምላክ የዱር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ከምድር ሠርቶ ነበር፤ ለእያንዳንዳቸውም ምን ስም እንደሚያወጣላቸው ለማየት ወደ አዳም አመጣቸው። አዳም ሕይወት ላላቸው ፍጥረታት ሁሉ ያወጣላቸው ስም መጠሪያቸው ሆነ። ስለዚህ አዳም ለከብቶች፣ ለሰማይ ወፎች፣ ለዱር አራዊት ሁሉ ስም አወጣላቸው። ይሁን እንጂ ለአዳም ተስማሚ ረዳት አልተገኘለትም ነበር። እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ላይ ከባድ እንቅልፍ ጣለበት፤ አንቀላፍቶም ሳለ ከጐድኑ አንዲት ዐጥንት ወስዶ፣ ስፍራውን በሥጋ ሞላው። እግዚአብሔር አምላክ ከአዳም የወሰዳትን ዐጥንት ሴት አድርጎ ሠራት፤ ወደ አዳምም አመጣት። አዳምም እንዲህ አለ፤ “እነሆ፤ ይህች ዐጥንት ከዐጥንቴ፣ ሥጋም ከሥጋዬ ናት። ከወንድ ተገኝታለችና ‘ሴት’ ትባል።” ስለዚህ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ ከሚስቱ ጋራ ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። አዳምና ሚስቱ፣ ሁለቱም ዕራቍታቸውን ነበሩ፤ ይሁን እንጂ አይተፋፈሩም ነበር።
ዘፍጥረት 2 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 2
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 2:15-25
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች