የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፍጥረት 2:1-17

ዘፍጥረት 2:1-17 NASV

የሰማያትና የምድር፣ በውስጣቸውም ያሉት ሁሉ አፈጣጠር በዚህ ሁኔታ ተከናወነ። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ይሠራ የነበረውን ሥራ በሰባተኛው ቀን ላይ ፈጽሞ ነበር፤ ስለዚህ ከሠራው ሥራ ሁሉ በሰባተኛው ቀን ዐረፈ። እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰባተኛውን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም፤ ካከናወነው የመፍጠር ሥራው ሁሉ ያረፈው በሰባተኛው ቀን ነውና። እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ሰማያትንና ምድርን በፈጠረ ጊዜ የተከናወኑት እንደዚህ ነበረ፤ እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ሰማያትንና ምድርን ሲፈጥር የሜዳ ቡቃያ ገና በምድር ላይ አልታየም፤ የሜዳ ተክልም ገና አልበቀለም፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) በመሬት ላይ ገና ዝናብ አላዘነበም ነበር፤ ምድርንም የሚያለማ ሰው አልነበረም። ነገር ግን ውሃ ከመሬት እየመነጨ የምድርን ገጽ ያረሰርስ ነበር። እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ከምድር ዐፈር ወስዶ ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ። እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) በምሥራቅ፣ በዔድን የአትክልት ስፍራ አዘጋጀ፤ ያበጀውንም ሰው በዚያ አኖረው። እግዚአብሔር አምላክም (ያህዌ ኤሎሂም) ለዐይን የሚያስደስት ለመብልም መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከምድር አበቀለ፤ በአትክልቱ ቦታ መካከልም የሕይወት ዛፍ ነበረ፤ እንዲሁም መልካምና ክፉን መለየት የሚያስችለው የዕውቀት ዛፍ ነበረ። የአትክልት ስፍራውን የሚያጠጣ ወንዝ ከዔድን ይፈስስ ነበር፤ ከዚያም በአራት ተከፍሎ ይወጣ ነበር። የመጀመሪያው፣ ወርቅ በሚገኝበት በሐዊላ ምድር ዙሪያ ሁሉ የሚፈስሰው የፊሶን ወንዝ ነው። ኤውላጥ ምርጥ የሆነ ወርቅ፣ መልካም መዐዛ ያለው ከርቤና የከበረ ድንጋይ የሚገኙበት ምድር ነው። ሁለተኛው፣ በኢትዮጵያ ምድር ዙሪያ ሁሉ የሚፈስሰው የግዮን ወንዝ ነው። ሦስተኛው፣ ከአሦር በስተ ምሥራቅ የሚፈስሰው የጤግሮስ ወንዝ ሲሆን፣ አራተኛው የኤፍራጥስ ወንዝ ነው። እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ሰውን ወስዶ እንዲያለማትና እየተንከባከበ እንዲጠብቃት በዔድን የአትክልት ስፍራ አስቀመጠው። እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ሰውን እንዲህ በማለት አዘዘው፤ “በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ትበላለህ። ነገር ግን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ ቀን በርግጥ ትሞታለህ።”

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}