ዘፍጥረት 18
18
ሦስቱ እንግዶች
1ቀትር ላይ አብርሃም በመምሬ ትልልቅ ዛፎች አቅራቢያ በምትገኘው ድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር ተገለጠለት፤ 2ቀና ብሎም ሲመለከት፣ ሦስት ሰዎች ቆመው አየ፤ ወዲያውም ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ፣ ፈጥኖ ወደ ሰዎቹ ሄደ፤ ወደ መሬት ዝቅ ብሎም እጅ ነሣ።
3አብርሃምም እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ፤#18፥3 ወይም ጌታ ሆይ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፣ ባሪያህን ዐልፈህ አትሂድ፤ 4ጥቂት ውሃ ይምጣላችሁና እግራችሁን ታጠቡ፤ እዚህም ከዛፉ ሥር ዐረፍ በሉ። 5ወደ እኔ ወደ አገልጋያችሁ ከመጣችሁ፣ እህል ቀምሳችሁ ትበረቱ ዘንድ ምግብ ላቅርብላችሁና ጕዟችሁን ትቀጥላላችሁ።”
እነርሱም፣ “መልካም፤ እንዳልኸው አድርግ” አሉት።
6አብርሃም በፍጥነት ሣራ ወዳለችበት ወደ ድንኳኑ ገብቶ፣ “ቶሎ ብለሽ ሦስት መስፈሪያ#18፥6 22 ሊትር ገደማ ይሆናል። ስልቅ ዱቄት አቡኪና ቂጣ ጋግሪ” አላት።
7ከዚያም ወደ መንጋው በጥድፊያ ሄዶ፣ አንድ ፍርጥም ያለ ሥጋው ገር የሆነ ጥጃ መርጦ ለአገልጋዩ ሰጠው፤ አገልጋዩም ጥጃውን ዐርዶ አዘጋጀው። 8አብርሃምም ርጎ፣ ወተትና የተዘጋጀውን የጥጃ ሥጋ አቀረበላቸው፤ ሲበሉም ዛፉ ሥር አጠገባቸው ቆሞ ነበር።
9እነርሱም አብርሃምን፣ “ሚስትህ ሣራ የት አለች?” ብለው ጠየቁት።
እርሱም፣ “ድንኳን ውስጥ ናት” አላቸው።
10 እግዚአብሔርም፣#18፥10 ዕብራይስጡ ከዚያም እርሱ ይለዋል። “ጊዜው ሲደርስ በርግጥ በዚህ ጊዜ በሚቀጥለው ዓመት እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልዳለች” አለው።
ሣራም በዚህ ጊዜ ከበስተጀርባው ካለው ከድንኳኑ ደጃፍ ሆና ትሰማ ነበር። 11በዚያ ጊዜ አብርሃምና ሣራ አርጅተው፣ ዕድሜያቸው ገፍቶ ነበር፤ ሣራም ልጅ የመውለጃዋ ዕድሜ ዐልፎ ነበር። 12ሣራ በልቧ፣ “ካረጀሁና ጌታዬም#18፥12 ወይም ባሌ ከደከመ በኋላ በዚህ ነገር መደሰት ይሆንልኛል?” ብላ ሣቀች።
13 እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ሣራ፣ ‘ካረጀሁ በኋላ ልጅ እንዴት አድርጌ እወልዳለሁ’ ስትል ለምን ሣቀች? 14ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? ጊዜው ሲደርስ እመለሳለሁ፤ ሣራም ልጅ ይኖራታል።”
15ሣራ ስለ ፈራች፣ “ኧረ አልሣቅሁም” ብላ ዋሸች።
እርሱ ግን፣ “ሣቅሽ እንጂ” አላት።
አብርሃም ስለ ሰዶም ማለደ
16ሰዎቹም ለመሄድ ሲነሡ፣ ቍልቍል ወደ ሰዶም ተመለከቱ፤ አብርሃምም ሊሸኛቸው ዐብሯቸው ወጣ። 17እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ “እኔ የማደርገውን ነገር ከአብርሃም እሰውራለሁን? 18አብርሃም በእውነት ታላቅና ብርቱ ሕዝብ ይሆናል፤ አሕዛብ ሁሉ በርሱ ይባረካሉ። 19ትክክለኛና ጽድቅ የሆነውን በማድረግ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከርሱ በኋላ ቤተ ሰቦቹን እንዲያዝዝ መርጬዋለሁ፤ ይኸውም እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠው ተስፋ ሁሉ እንዲፈጸም ነው።”
20ደግሞም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “በሰዶምና በገሞራ ላይ የሚሰማው ጩኸት እጅግ በዝቷል፤ ኀጢአታቸውም እጅግ ከፍቷል፤ 21አድራጎታቸው እኔ ዘንድ እንደ ደረሰው ጩኸት መሆኑን ለማየት ወደዚያው እወርዳለሁ፤ እንደዚያ ካልሆነም ዐውቃለሁ።”
22ሰዎቹም ፊታቸውን ወደ ሰዶም አቅንተው ሄዱ፤ አብርሃም ግን በእግዚአብሔር ፊት እንደ ቆመ ነበር።#18፥22 ከማሶሬቲኩ ጽሑፍ ጋራ ተመሳሳይ ሲሆን የጥንት ዕብራውያን የጻፉት ትውፊት ግን እግዚአብሔር ግን በአብርሃም ፊት እንደ ቆመ ነበር ይላል። 23አብርሃምም ወደ እርሱ ቀረብ ብሎ እንዲህ አለ፤ “በርግጥ ጻድቁን ከኀጢአተኛው ጋራ ዐብረህ ታጠፋለህን? 24ዐምሳ ጻድቃን በከተማዪቱ ቢገኙ፣ በውኑ ነዋሪዎቹን ሁሉ ታጠፋለህን? በውስጧ ለሚገኙ ዐምሳ ጻድቃን ስትል ከተማዪቱን ይቅር አትልምን?#18፥24 ወይም ይቅርታ ማድረግ ሊሆን ይችላል፤ ይህም በ26 ላይ ያለውንም ጨምሮ ነው። 25እንዲህስ አይሁን፤ ጻድቁን ከኀጢአተኛው ጋራ እንዴት ትገድለዋለህ? ይህን የመሰለው አድራጎት ከአንተ ይራቅ፤ የምድር ሁሉ ዳኛ#18፥25 ወይም ገዥ በቅን አይፈርድምን?”
26 እግዚአብሔርም፣ “በሰዶም ከተማ ዐምሳ ጻድቃን ባገኝ ለእነርሱ ስል አገሪቱን በሞላ እምራለሁ” አለ።
27ደግሞም አብርሃም እንዲህ አለ፤ “እኔ ከንቱ፣ ትቢያና ዐመድ ሆኜ ሳለሁ ከጌታ ጋራ ለመናገር አንዴ ደፍሬአለሁ፤ 28ለመሆኑ ከዐምሳው ጻድቃን ዐምስት ቢጐድሉ በዐምስቱ ሰዎች ምክንያት መላ ከተማዋን ታጠፋለህን?”
እርሱም፣ “አርባ ዐምስት ጻድቃን ባገኝ አላጠፋትም” አለ።
29አብርሃምም እንደ ገና፣ “ምናልባት አርባ ጻድቃን ቢገኙስ?” አለ።
እርሱም፣ “ለአርባው ስል እምራታለሁ” አለ።
30ደግሞም አብርሃም፣ “ጌታዬ አይቈጣ፤ እባክህ ልናገር፤ ሠላሳ ጻድቃን ብቻ ቢገኙስ?”
እርሱም፣ “ሠላሳ ባገኝ አላጠፋትም” ብሎ መለሰ።
31አብርሃምም፣ “ከጌታዬ ጋራ እናገር ዘንድ መቼም አንዴ ደፍሬአለሁና ምናልባት ሃያ ብቻ ቢገኙስ?” አለ።
እርሱም፣ “ሃያ ቢገኙ፣ ለእነርሱ ስል እምራታለሁ” አለ።
32አብርሃምም፣ “ጌታዬ አይቈጣ፤ አንድ ጊዜ ብቻ ልናገር፤ ምናልባት ዐሥር ብቻ ቢገኙስ?” አለ።
እርሱም “ስለ ዐሥሩ ስል አላጠፋትም” ብሎ መለሰ።
33 እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋራ ንግግሩን ከጨረሰ በኋላ ሄደ፤ አብርሃምም ወደ ቤቱ ተመለሰ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.