ሰዎቹም ለመሄድ ሲነሡ፣ ቍልቍል ወደ ሰዶም ተመለከቱ፤ አብርሃምም ሊሸኛቸው ዐብሯቸው ወጣ። እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ “እኔ የማደርገውን ነገር ከአብርሃም እሰውራለሁን? አብርሃም በእውነት ታላቅና ብርቱ ሕዝብ ይሆናል፤ አሕዛብ ሁሉ በርሱ ይባረካሉ። ትክክለኛና ጽድቅ የሆነውን በማድረግ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከርሱ በኋላ ቤተ ሰቦቹን እንዲያዝዝ መርጬዋለሁ፤ ይኸውም እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠው ተስፋ ሁሉ እንዲፈጸም ነው።” ደግሞም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “በሰዶምና በገሞራ ላይ የሚሰማው ጩኸት እጅግ በዝቷል፤ ኀጢአታቸውም እጅግ ከፍቷል፤ አድራጎታቸው እኔ ዘንድ እንደ ደረሰው ጩኸት መሆኑን ለማየት ወደዚያው እወርዳለሁ፤ እንደዚያ ካልሆነም ዐውቃለሁ።” ሰዎቹም ፊታቸውን ወደ ሰዶም አቅንተው ሄዱ፤ አብርሃም ግን በእግዚአብሔር ፊት እንደ ቆመ ነበር። አብርሃምም ወደ እርሱ ቀረብ ብሎ እንዲህ አለ፤ “በርግጥ ጻድቁን ከኀጢአተኛው ጋራ ዐብረህ ታጠፋለህን? ዐምሳ ጻድቃን በከተማዪቱ ቢገኙ፣ በውኑ ነዋሪዎቹን ሁሉ ታጠፋለህን? በውስጧ ለሚገኙ ዐምሳ ጻድቃን ስትል ከተማዪቱን ይቅር አትልምን? እንዲህስ አይሁን፤ ጻድቁን ከኀጢአተኛው ጋራ እንዴት ትገድለዋለህ? ይህን የመሰለው አድራጎት ከአንተ ይራቅ፤ የምድር ሁሉ ዳኛ በቅን አይፈርድምን?” እግዚአብሔርም፣ “በሰዶም ከተማ ዐምሳ ጻድቃን ባገኝ ለእነርሱ ስል አገሪቱን በሞላ እምራለሁ” አለ። ደግሞም አብርሃም እንዲህ አለ፤ “እኔ ከንቱ፣ ትቢያና ዐመድ ሆኜ ሳለሁ ከጌታ ጋራ ለመናገር አንዴ ደፍሬአለሁ፤ ለመሆኑ ከዐምሳው ጻድቃን ዐምስት ቢጐድሉ በዐምስቱ ሰዎች ምክንያት መላ ከተማዋን ታጠፋለህን?” እርሱም፣ “አርባ ዐምስት ጻድቃን ባገኝ አላጠፋትም” አለ። አብርሃምም እንደ ገና፣ “ምናልባት አርባ ጻድቃን ቢገኙስ?” አለ። እርሱም፣ “ለአርባው ስል እምራታለሁ” አለ። ደግሞም አብርሃም፣ “ጌታዬ አይቈጣ፤ እባክህ ልናገር፤ ሠላሳ ጻድቃን ብቻ ቢገኙስ?” እርሱም፣ “ሠላሳ ባገኝ አላጠፋትም” ብሎ መለሰ። አብርሃምም፣ “ከጌታዬ ጋራ እናገር ዘንድ መቼም አንዴ ደፍሬአለሁና ምናልባት ሃያ ብቻ ቢገኙስ?” አለ። እርሱም፣ “ሃያ ቢገኙ፣ ለእነርሱ ስል እምራታለሁ” አለ። አብርሃምም፣ “ጌታዬ አይቈጣ፤ አንድ ጊዜ ብቻ ልናገር፤ ምናልባት ዐሥር ብቻ ቢገኙስ?” አለ። እርሱም “ስለ ዐሥሩ ስል አላጠፋትም” ብሎ መለሰ። እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋራ ንግግሩን ከጨረሰ በኋላ ሄደ፤ አብርሃምም ወደ ቤቱ ተመለሰ።
ዘፍጥረት 18 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 18
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 18:16-33
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos