ዘፍጥረት 17:1-27

ዘፍጥረት 17:1-27 NASV

አብራም ዕድሜው 99 ዓመት በሆነ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ተገልጦለት እንዲህ አለው፤ “እኔ ሁሉን ቻይ አምላክ ነኝ፤ በፊቴ ተመላለስ፤ ነቀፋም አይኑርብህ፤ በእኔና በአንተ መካከል የተመሠረተውን ኪዳን አጸናለሁ፤ ዘርህንም እጅግ አበዛለሁ።” አብራም በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “እነሆ፤ የምገባልህ ኪዳን ይህ ነው፤ የብዙ ሕዝቦች አባት ትሆናለህ። ከእንግዲህ ወዲያ ስምህ አብራም መባሉ ቀርቶ አብርሃም ይሆናል፤ የብዙ ሕዝቦች አባት አድርጌሃለሁና። ዘርህን እጅግ አበዛለሁ፤ ብዙ ሕዝብም አደርግሃለሁ፤ ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ። በእኔና በአንተ፣ ከአንተም በኋላ ከዘርህ ጋራ ከትውልድ እስከ ትውልድ የዘላለም ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤ በዚህም የአንተና ከአንተም በኋላ የዘርህ አምላክ እሆናለሁ። ይህችን አሁን በእንግድነት የምትኖርባትን የከነዓንን ምድር በሙሉ ለአንተና ከአንተም በኋላ ለዘርህ ለዘላለም ርስት አድርጌ እሰጣቸዋለሁ፤ አምላካቸውም እሆናለሁ።” ከዚያም እግዚአብሔር አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “በአንተም በኩል፣ አንተና ከአንተ በኋላ የሚመጣው ዘርህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ኪዳኔን ትጠብቃላችሁ። አንተና ከአንተም በኋላ የሚመጣው ዘርህ የምትጠብቁት ኪዳን ይህ ነው፤ በመካከላችሁ ያለ ወንድ ሁሉ ይገረዝ። ስለዚህ ሁላችሁም ሸለፈታችሁን ትገረዛላችሁ፤ ይህም በእኔና በእናንተ መካከል ላለው ኪዳን ምልክት ይሆናል። የሚመጣውም ትውልድ ሁሉ፣ ማንኛውም ወንድ ልጅ፣ ስምንት ቀን ሲሞላው ይገረዝ፤ እንደዚሁም በቤትህ የተወለደውና ከውጭ በገንዘብ የተገዛ ባዕድ ሁሉ ይገረዝ። በቤትህ የተወለደም ሆነ በገንዘብህ የተገዛ ሁሉ መገረዝ አለበት፤ በሥጋችሁ የሚፈጸመው ይህ ኪዳኔ የዘላለም ኪዳን ይሆናል። የሥጋ ሸለፈቱን ያልተገረዘ ማንኛውም ወንድ ኪዳኔን በማፍረሱ ከወገኖቹ ይወገድ።” እግዚአብሔር አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ሦራን ከእንግዲህ ሦራ ብለህ አትጠራትም፤ ስሟ ከዛሬ ጀምሮ ሣራ ይሁን። እኔ እባርካታለሁ ከርሷም ወንድ ልጅ እሰጥሃለሁ፤ የብዙም ሕዝቦች እናት ትሆን ዘንድ እባርካታለሁ፤ የሕዝቦችም ነገሥታት ከርሷ ይወጣሉ።” አብርሃምም በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ፤ ሣቀና በልቡ፣ “እንዲያው ምንስ ቢሆን የመቶ ዓመት ሽማግሌ የልጅ አባት መሆን ይችላልን? ሣራስ በዘጠና ዓመቷ ልጅ መውለድ ትችላለችን?” አለ። አብርሃም እግዚአብሔርን፣ “እስማኤልን ብቻ ባርከህ ባኖርህልኝ” አለው። እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “ይሁን ዕሺ፤ ነገር ግን ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ይሥሐቅ ብለህ ትጠራዋለህ፤ እኔም ከርሱ በኋላ ለዘሩ ሁሉ የሚሆን የዘላለም ኪዳን ከርሱ ጋራ እገባለሁ። ስለ እስማኤልም ቢሆን ልመናህን ሰምቼሃለሁ፤ እርሱንም እባርከዋለሁ፤ ፍሬያማም አደርገዋለሁ፤ እጅግም አበዛዋለሁ፤ የዐሥራ ሁለት አለቆች አባት ይሆናል፤ ታላቅም ሕዝብ አደርገዋለሁ። ኪዳኔን ግን የዛሬ ዓመት በዚሁ ጊዜ ሣራ ከምትወልድልህ ልጅ፣ ከይሥሐቅ ጋራ አደርጋለሁ።” እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋራ መነጋገሩን ከፈጸመ በኋላ ወደ ላይ ወጣ። በዚያችም ዕለት አብርሃም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ልጁን እስማኤልን፣ በቤቱ ውስጥ የተወለዱትንና ከውጭ በገንዘቡ የገዛቸውን ወንዶች በሙሉ ሸለፈታቸውን ገረዛቸው። አብርሃም ሸለፈቱን ሲገረዝ ዕድሜው 99 ዓመት ነበር። ልጁም እስማኤል ሸለፈቱን ሲገረዝ 13 ዓመቱ ነበር። አብርሃምና ልጁ እስማኤል፣ ሁለቱም በዚያ ቀን ተገረዙ። በአብርሃም ቤት ያሉ ወንዶች ሁሉ፣ በቤቱ የተወለዱትም ሆኑ ከውጭ በገንዘብ የተገዙ ከርሱ ጋራ ተገረዙ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}