ዘፍጥረት 15:12-21

ዘፍጥረት 15:12-21 NASV

ፀሓይ ልትገባ ስትል አብራም እንቅልፍ ወሰደው፤ የሚያስፈራም ድቅድቅ ጨለማ መጣበት። እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “ዘርህ በባዕድ አገር መጻተኛ እንደሚሆን በርግጥ ዕወቅ፤ አራት መቶ ዓመትም በባርነት ተረግጦ ይገዛል። ነገር ግን በባርነት የሚገዛቸውን ሕዝብ እቀጣዋለሁ፤ ከዚያም ብዙ ሀብት ይዘው ይወጣሉ። አንተ ግን ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ፤ ዕድሜም ጠግበህ ወደ መቃብር ትወርዳለህ፤ በአራተኛውም ትውልድ ዘርህ ወደዚህ ምድር ይመለሳል፤ የአሞራውያን ኀጢአት ገና ጽዋው አልሞላምና።” ፀሓይ ገብታ ከጨለመ በኋላ የምድጃ ጢስና የሚንበለበል ፋና ታየ፤ በተከፈለውም ሥጋ መካከል ዐለፈ። በዚያ ዕለት እግዚአብሔር ለአብራም እንዲህ ሲል ኪዳን ገባለት፤ “ከግብጽ ወንዝ ጀምሮ እስከ ታላቁ የኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ያለውን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ፤ የምሰጣቸውም የቄናውያንን፣ የቄኔዛውያንን፣ የቃድሞናውያንን፣ የኬጢያውያንን፣ የፌርዛውያንን፣ የራፋይምን፣ የአሞራውያንን፣ የከነዓናውያንን፣ የጌርጌሳውያንንና የኢያቡሳውያንን ምድር ነው።”

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}