የኖኅ ልጆች የሴም፣ የካምና የያፌት ትውልድ ይህ ነው፤ እነርሱም ራሳቸው ከጥፋት ውሃ በኋላ ወንዶች ልጆችን ወለዱ። የያፌት ልጆች፦ ጋሜር፣ ማጎግ፣ ማዴ፣ ያዋን፣ ቶቤል፣ ሞሳሕ፣ ቴራስ ናቸው። የጋሜር ልጆች፦ አስከናዝ፣ ራፋት፣ ቴርጋማ ናቸው። የያዋን ልጆች፦ ኤሊሳ፣ ተርሴስ፣ ኪቲም፣ ሮዲኢ ናቸው። ከእነዚህም በየነገዳቸው፣ በየጐሣቸውና በየቋንቋቸው ተከፋፍለው በባሕር ዳርና በደሴቶች፣ በየምድራቸው የሚኖሩ ሕዝቦች ወጡ። የካም ልጆች፦ ኵሽ፣ ምጽራይም፣ ፉጥ፣ ከነዓን ናቸው። የኵሽ ልጆች፦ ሳባ፣ ኤውላጥ፣ ሰብታ፣ ራዕማ፣ ሰበቅታ ናቸው። የራዕማ ልጆች፦ ሳባ፣ ድዳን ናቸው። ኵሽ የናምሩድ አባት ነበረ፤ ናምሩድም በምድር ላይ ኀያል ሰው እየሆነ ሄደ። በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ብርቱ ዐዳኝ ነበረ፤ ስለዚህም፣ “በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እንደ ናምሩድ ብርቱ ዐዳኝ” ይባል ነበር። የግዛቱም የመጀመሪያ ከተሞች፦ ባቢሎን፣ ኦሬክ፣ አርካድና ካልኔ ናቸው፤ እነዚህ በ ሰናዖር ምድር ነበሩ። ከዚያም ምድር ወደ አሦር ወጥቶ ነነዌን፣ ረሆቦትን፣ ካለህን እንዲሁም በነነዌና በካለህ መካከል ሬስን ቈረቈረ፤ ታላቁንም ከተማ መሠረተ። ምጽራይም፦ የሉዳማውያን፣ የዕሚማውያን፣ ላህቢያውያን፣ የነፍታሌማውያን፣ የፈትሩሲማውያን፣ ፍልስጥኤማውያን የተገኙባቸው የኮስሉሂማውያን፣ የቀፍቶሪማውያን አባት ነበረ። ከነዓንም፦ የበኵር ልጁ የሲዶን፣ የኬጢያውያን፣ የኢያቡሳውያን፣ የአሞራውያን፣ የጌርሳውያን አባት ነበረ፤ እንዲሁም የኤዊያውያን፣ የዑር ኬዋናውያን፣ የሲኒያውያን፣ የአራዴዎናውያን፣ የሰማሪናውያን፣ የአማቲያውያን አባት ነበረ። ከጊዜ በኋላ የከነዓን ጐሣዎች በየስፍራው ተሠራጩ፤ የከነዓን ወሰን ከሲዶና አንሥቶ በጌራራ በኩል እስከ ጋዛ ይደርሳል፤ ከዚያም በሰዶም በኩል ገሞራን፣ አዳማንና ሰቦይን ይዞ እስከ ላሣ ይዘልቃል። እነዚህም በየጐሣቸውና በየቋንቋቸው፣ በየምድራቸውና በየነገዳቸው ይኖሩ የነበሩ የካም ዝርያዎች ናቸው። ለያፌት ታላቅ ወንድም ለሴም ደግሞ ወንዶች ልጆች ተወለዱለት፤ እርሱም የዔቦር ልጆች ሁሉ ቅደመ አያት ነው። የሴም ልጆች፦ ኤላም፣ አሦር፣ አርፋክስድ፣ ሉድ፣ አራም ናቸው። የአራም ልጆች፦ ዑፅ፣ ሁል፣ ጌቴር፣ ሞሶሕ ናቸው። አርፋክስድ ሳላን ወለደ፤ ሳላም ዔቦርን ወለደ። ለዔቦርም ሁለት ወንዶች ልጆች ተወለዱለት፤ አንደኛው ልጅ በዘመኑ ምድር ተከፍላ ስለ ነበር ፍሌቅ ተባለ፤ ወንድሙም ዮቅጣን ተባለ። ዮቅጣንም፦ የኤልሞሳድ፣ የሣሌፍ፣ የሐስረሞት፣ የያራሕ፣ የሀደራም፣ የአውዛል፣ የደቅላ አባት ነበረ፤ እንዲሁም የዖባል፣ የአቢማኤል፣ የሳባ፣ የኦፊር፣ የኤውላጥ፣ የዮባል አባት ነበረ፤ እነዚህ ሁሉ የዮቅጣን ልጆች ናቸው። መኖሪያ ስፍራቸውም እስከ ሶፋር ድረስ ይዘልቃል። እነዚህም በየጐሣቸውና በየቋንቋቸው፣ በየምድራቸውና በየነገዳቸው ይኖሩ የነበሩ የሴም ዝርያዎች ናቸው። የኖኅ ወንዶች ልጆች ጐሣዎች እንደ ትውልዳቸው በየነገዳቸው እነዚህ ነበሩ። ከጥፋት ውሃ በኋላ ሕዝቦች በምድር ላይ የተሠራጩት ከእነዚሁ ነው።
ዘፍጥረት 10 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 10
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 10:1-32
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos