የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ገላትያ 2:1-10

ገላትያ 2:1-10 NASV

ከዐሥራ አራት ዓመት በኋላም፣ ዳግመኛ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣሁ፤ በዚህ ጊዜ ከበርናባስ ጋር ነበርሁ፤ ቲቶንም ይዤው ሄጄ ነበር። ካገኘሁትም መገለጥ የተነሣ ወደዚያ ሄድሁ፤ በአሕዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል ለእነርሱም ገለጥሁላቸው። ይሁን እንጂ፣ ምናልባት በከንቱ እየሮጥሁ ወይም ሮጬ እንዳይሆን በመሥጋት፣ ዋነኞች ለሚመስሉት ብቻ በግል ይህን አስታወቅኋቸው። ከእኔ ጋር የነበረው ቲቶ እንኳ የግሪክ ሰው ቢሆንም፣ እንዲገረዝ አልተገደደም ነበር። ይህ ጕዳይ የተነሣው አንዳንድ ሐሰተኞች ወንድሞች በክርስቶስ ኢየሱስ ያገኘነውን ነጻነት ሊሰልሉና ባሪያዎች ሊያደርጉን ወደ እኛ ሾልከው በመግባታቸው ነው። ለእነዚህ ሰዎች ለአንድ አፍታ እንኳ አልተገዛንላቸውም፤ ይኸውም፣ የወንጌል እውነት ከእናንተ ጋር ጸንቶ እንዲኖር ነው። ዋነኛ መስለው ስለሚታዩት ሰዎች ማንነት እኔን አይገደኝም፤ እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ አያደላም፤ እነዚህም ሰዎች ለመልእክቴ የጨመሩልኝ ነገር የለም። ነገር ግን ጴጥሮስ ለተገረዙት ወንጌልን እንዲሰብክ ዐደራ እንደ ተሰጠው፣ እኔም ላልተገረዙት ወንጌልን እንድሰብክ ዐደራ እንደ ተሰጠኝ ተገነዘቡ፤ ጴጥሮስን ለአይሁድ ሐዋርያ እንዲሆን የሠራ እግዚአብሔር፣ በእኔ የአሕዛብ ሐዋርያዊ አገልግሎትም ሠርቷል። እንደ አዕማድ የሚቈጠሩት ያዕቆብ፣ ጴጥሮስና ዮሐንስም የተሰጠኝን ጸጋ ባስተዋሉ ጊዜ፣ ለእኔና ለበርናባስ የትብብር ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤ ከዚያም እኛ ወደ አሕዛብ፣ እነርሱ ደግሞ ወደ አይሁድ እንድንሄድ ተስማሙ። አጥብቀው ዐደራ ያሉን ድኾችን ማሰባችንን እንዳናቋርጥ ብቻ ነው፤ እኔም ይህንኑ ለማድረግ ጓጕቼ ነበር።