የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሕዝቅኤል 4

4
የኢየሩሳሌም መከበብ ምሳሌ
1“አንተ፣ የሰው ልጅ ሆይ፤ አንድ የሸክላ ጡብ ወስደህ ከፊት ለፊትህ አስቀምጥ፤ የኢየሩሳሌምን ከተማ ካርታ ሥራበት። 2ከዚያም በወታደር እንደሚከበብ ክበባት፤ ምሽግ ሥራባት፤ ዐፈር ደልድልባት፤ ጦር ሰፈሮችን ቀብቅብባት፤ ቅጥር መደርመሻ ግንዶችንም በዙሪያዋ አስቀምጥባት። 3የብረት ምጣድ ወስደህ በአንተና በከተማዪቱ መካከል እንደ ብረት ቅጥር አቁመው፤ ፊትህንም ወደ እርሷ አዙር፤ የተከበበች ትሆናለች፤ አንተም ትከብባታለህ። ይህም ለእስራኤል ቤት ምልክት ይሆናል።
4“አንተ በግራ ጐንህ ተኛ፤ የእስራኤልም ቤት ኀጢአት በአንተ ላይ#4፥4 ወይም በአንተ በኩል ይሁን ይሁን፤ በዚህ ጐንህ በተኛህበት ቀን ቍጥር ኀጢአታቸውን ትሸከማለህ። 5እነርሱ ኀጢአት ባደረጉባቸው ዓመታት መጠን የቀን ቍጥር መድቤብሃለሁ። ስለዚህ ሦስት መቶ ዘጠና ቀን የእስራኤልን ቤት ኀጢአት ትሸከማለህ።
6“ይህን ከፈጸምህ በኋላ ደግሞ በቀኝ ጐንህ ተኝተህ የይሁዳን ቤት ኀጢአት ትሸከማለህ፤ ለእያንዳንዱ ዓመት አንድ አንድ ቀን በማድረግ አርባ ቀን መድቤብሃለሁ። 7ፊትህን ወደ ኢየሩሳሌም ከበባ ታዞራለህ፣ በዕራቍት ክንድህ ትንቢት ተናገርባት። 8የከበባህን ወራት እስክትፈጽም ድረስ ከአንዱ ጐን ወደ ሌላው መገላበጥ እንዳትችል በገመድ አስርሃለሁ።
9“ስንዴና ገብስ፣ ባቄላና ምስር እንዲሁም ዘንጋዳና ጠመዥ ወስደህ በአንድ ሸክላ ውስጥ አስቀምጥ፤ ከዚያም ለራስህ እንጀራ ጋግር፤ ሦስት መቶ ዘጠና ቀን በጐንህ በምትተኛበት ጊዜ ትመገበዋለህ። 10በየቀኑ የምትበላውን እህል ሃያ ሃያ ሰቅል መዝነህ አስቀምጥ፤ በተወሰነ ጊዜ ትበላዋለህ፤ 11የምትጠጣውንም ውሃ አንድ#4፥11 አንድ ስድስተኛ (1/6ኛ) ኢን ግማሽ ሊትር ያህል ነው። ስድስተኛ ኢን ለክተህ አስቀምጥ፤ በተወሰነ ጊዜ ትጠጣዋለህ። 12የገብስ ዕንጎቻ እንደምትበላ አድርገህ ትበላለህ፤ የሰውንም ዐይነ ምድር አንድደህ በሕዝብ ፊት ጋግረው።” 13እግዚአብሔርም፣ “በዚህ ሁኔታ የእስራኤል ሕዝብ እነርሱን በምበትንበት በአሕዛብ መካከል ርኩስ ምግብ ይበላሉ” አለ።
14እኔም፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ወይኔ! ከቶ ረክሼ አላውቅም፤ ከልጅነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ጥንብ ወይም አውሬ የጣለውን በልቼ አላውቅም፤ ርኩስ ሥጋም በአፌ አልገባም” አልሁ።
15እርሱም፣ “መልካም ነው፤ በሰው ዐይነ ምድር ሳይሆን፤ እንጀራህን በኩበት እንድትጋግር ፈቅጄልሃለሁ” አለኝ።
16ደግሞም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ የኢየሩሳሌምን የምግብ ምንጭ አደርቃለሁ፤ ሕዝቡም የተወሰነ ምግብ በጭንቀት ይበላል፤ የተመጠነ ውሃም በሥጋት ይጠጣል። 17የምግብና የውሃ ዕጥረት ስለሚኖር፣ እርስ በርስ ሲተያዩ ይደነግጣሉ፤ ከኀጢአታቸውም የተነሣ#4፥17 ወይም በኀጢአታቸው መንምነው ይጠፋሉ መንምነው ይጠፋሉ።

Currently Selected:

ሕዝቅኤል 4: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ