ሕዝቅኤል 29
29
በግብፅ ላይ የተነገረ ትንቢት
1በዐሥረኛው ዓመት፣ በዐሥረኛው ወር፣ በዐሥራ ሁለተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2“የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ ግብፅ ንጉሥ ወደ ፈርዖን አዙር፤ በእርሱና በግብፅ ሁሉ ላይ ትንቢት ተናገር፤ 3እንዲህም ብለህ ተናገረው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።
“ ‘በወንዞችህ መካከል የምትተኛ አንተ ታላቅ አውሬ፣
የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን፤ በአንተ ላይ ተነሥቻለሁ።
“የአባይ ወንዝ የእኔ ነው፤
ለራሴም ሠርቼዋለሁ” ትላለህ።
4ነገር ግን በመንጋጋህ መንጠቆ አስገባለሁ፤
የወንዞችህን ዓሦች ከቅርፊትህ ጋር አጣብቃለሁ፤
ቅርፊትህ ላይ ከተጣበቁት ዓሦች ሁሉ ጋር፣
ከወንዞችህ ጐትቼ አወጣሃለሁ።
5አንተንና በወንዞችህ ያለውን ዓሣ ሁሉ፣
በምድረ በዳ እጥላለሁ።
በገላጣ መሬት ላይ ትወድቃለህ፤
የሚሰበስብህ፣ የሚያነሣህም አይኖርም።
ለምድር አራዊትና ለሰማይ ወፎች፣
ምግብ እንድትሆን አሳልፌ እሰጥሃለሁ።
6ከዚያም በግብፅ የሚኖሩ ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
“ ‘ለእስራኤል ቤት የሸንበቆ በትር ነበርህ፤ 7በእጃቸው ሲይዙህ ተሰንጥረህ ትከሻቸውን ወጋህ፤ ሲደገፉህም ተሰብረህ ጀርባቸውን አጐበጥህ።#29፥7 በሱርስቱም (በተጨማሪ ሰብዐ ሊቃናትና ቩልጌትን ይመ) እንዲሁ ሲሆን ዕብራይስጡ ግን ጀርባቸውን ቀጥ አደረግህ ይላል
8“ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሰይፍ አመጣብሃለሁ፤ ሰዎችህንና እንስሶቻቸውን እገድላለሁ። 9ግብፅ ባድማና ምድረ በዳ ትሆናለች፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
“ ‘ “የአባይ ወንዝ የእኔ ነው፤ እኔም ሠርቼዋለሁ” ብለሃልና፤ 10ስለዚህ በአንተ ላይ ተነሥቻለሁ፤ በወንዞችህ ላይ ተነሥቻለሁ፤ የግብፅንም ምድር ከሚግዶል እስከ አስዋን ከዚያም እስከ ኢትዮጵያ ወሰን ድረስ ፍርስራሽና ባድማ አደርጋታለሁ። 11የሰው እግርም ሆነ የእንስሳ ኰቴ በውስጧ አያልፍም፤ እስከ አርባ ዓመት ማንም አይኖርባትም። 12የግብፅን ምድር ከጠፉት ምድሮች መካከል እንደ አንዱ ባድማ አደርጋታለሁ፤ ከተሞቿም በፈራረሱት ከተሞች መካከል አርባ ዓመት ባድማ ይሆናሉ፤ ግብፃውያንንም በአሕዛብ መካከል እበትናቸዋለሁ፤ በአገሮችም መካከል እዘራቸዋለሁ።
13“ ‘ያም ሆኖ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከአርባ ዓመት በኋላ ግብፃውያንን ከተበተኑበት አገሮች መካከል እሰበስባቸዋለሁ። 14ከተማረኩበት አመጣቸዋለሁ፤ ወደ አባቶቻቸው ምድር ወደ ጳትሮስ እመልሳቸዋለሁ። 15ከመንግሥታት ሁሉ አነስተኛ ትሆናለች፤ ከሌሎችም አሕዛብ በላይ ራሷን ከፍ ማድረግ አትችልም። እጅግ ደካማ አደርጋታለሁ፤ ስለዚህ ሌሎችን አሕዛብ እንደ ገና መግዛት አትችልም። 16ግብፅ ከእንግዲህ ለእስራኤል ሕዝብ መታመኛ አትሆንም፤ ለርዳታ ወደ እርሷ ዘወር ባሉ ጊዜ ላደረጉት ኀጢአት ግን መታሰቢያ ትሆናለች። ከዚያም እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።’ ”
17በሃያ ሰባተኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 18“የሰው ልጅ ሆይ፤ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር አስቸጋሪ በሆነ ዘመቻ ሰራዊቱን በጢሮስ ላይ አንቀሳቀሰ፤ የሁሉም ራስ ተመልጧል፤ የሁሉም ትከሻ ተልጧል፤ ይሁን እንጂ እርሱና ሰራዊቱ በጢሮስ ላይ ካደረጉት ዘመቻ ያተረፉት ነገር የለም። 19ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ግብፅን ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እሰጣለሁ፤ ሀብቷን ሁሉ ያግዛል፤ ለሰራዊቱም ደመወዝ ይሆን ዘንድ ምድሪቱን ይበዘብዛል፤ ይመዘብራልም። 20እርሱና ሰራዊቱ ለእኔ በመልፋታቸው፣ ግብፅን ለድካሙ ዋጋ ሰጥቼዋለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
21“በዚያ ቀን ለእስራኤል ቤት ቀንድ#29፥21 ቀንድ በዚህ ቦታ ጥንካሬን ያመለክታል አበቅላለሁ፤ በመካከላቸውም አፍህን እከፍታለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።”
Currently Selected:
ሕዝቅኤል 29: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.