የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሕዝቅኤል 22

22
የኢየሩሳሌም ኀጢአት
1 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤
2“የሰው ልጅ ሆይ፤ አትፈርድባትምን? ደም በምታፈስሰው በዚህች ከተማ ላይ አትፈርድባትምን? ጸያፍ ተግባሯን ፊት ለፊት ንገራት፤ 3እንዲህም በላት፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በመካከልሽ ደምን በማፍሰስና ጣዖታትን በመሥራት ራስሽን የምታረክሺ፣ ፍርድንም በራስሽ ላይ የምታፈጥኚ ከተማ ሆይ፤ 4ባፈሰስሽው ደም በድለሻል፤ በሠራሽውም ጣዖት ረክሰሻል፤ ከዚህም የተነሣ ቀንሽን አቅርበሻል፤ ዕድሜሽንም አሳጥረሻል። ስለዚህ ለአሕዛብ መዘባበቻ፣ ለአገሩም ሁሉ መሣለቂያ አደርግሻለሁ። 5አንቺ የተዋረድሽና ሽብር የሞላብሽ ሆይ፤ በቅርብም በሩቅም ያሉ ይሣለቁብሻል።
6“ ‘እነሆ በመካከልሽ ያለ እያንዳንዱ የእስራኤል መስፍን ደም ለማፍሰስ ሥልጣኑን ይጠቀማል። 7አባቶችና እናቶች በውስጥሽ ተዋረዱ፤ መጻተኞች ተጨቈኑ፤ ድኻ አደጎችና መበለቶች ተንገላቱ። 8ንዋያተ ቅድሳቴን አቃለልሽ፤ ሰንበታቴንም አረከስሽ። 9ደምን ለማፍሰስ ወሬ የሚያቀብሉ በውስጥሽ አሉ፤ በኰረብታ ቤተ ጣዖት የተሠዋውን የሚበሉና ዝሙትን የሚፈጽሙ ሰዎች በመካከልሽ ይገኛሉ። 10የአባታቸውን መኝታ የሚደፍሩ ሰዎች በውስጥሽ አሉ፤ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ ባልሆኑበት በወር አበባቸው ጊዜ ሴቶችን በማስገደድ የሚደፍሩ በመካከልሽ ይገኛሉ። 11በውስጥሽ አንዱ የባልንጀራውን ሚስት ያባልጋል፤ ሌላውም የልጁን ሚስት ያስነውራል፤ ሌላው ደግሞ የገዛ እኅቱ የሆነችውን የአባቱን ልጅ ይደፍራል። 12በመካከልሽ ያሉ ሰዎች ደም ለማፍሰስ ጕቦ ይቀበላሉ፤ አንቺም ዐራጣና ከፍተኛ ወለድ#22፥12 ወይም ዐራጣና ወለድ በመውሰድ ከባልንጀራሽ የማይገባ ትርፍ ዘረፍሽ፤ እኔንም ረስተሻል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር
13“ ‘ያለ አግባብ ባገኘሽው ጥቅምና በመካከልሽ ባፈሰስሽው ደም ላይ እጄን አጨበጭባለሁ። 14እኔ ልቀጣሽ በምነሣበት ጊዜ፣ በልበ ሙሉነት መቆም ትችያለሽን? ወይስ እጅሽ ሊበረታ ይችላልን? እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፤ አደርገዋለሁም። 15በሕዝቦች መካከል እበትንሻለሁ፤ በየአገሩም እዘራሻለሁ፤ ከርኩሰትሽም አጠራሻለሁ። 16በሕዝቦች ዘንድ በምትረክሺበት ጊዜ፣#22፥16 ወይም ርስትሽን ለአንቺ በሰጠሁሽ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ።’ ”
17 የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 18“የሰው ልጅ ሆይ፤ የእስራኤል ቤት የብረት ዝቃጭ ሆነብኝ፤ ሁሉም በከውር ውስጥ ቀልጦ እንደሚቀር መዳብ፣ ቈርቈሮ፣ ብረትና እርሳስ ናቸው፤ እነዚህ ከብር የሚወጡ ዝቃጭ ናቸው። 19ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ ‘ሁላችሁም የብረት ዝቃጭ ስለ ሆናችሁ ወደ ኢየሩሳሌም እሰበስባችኋለሁ። 20ሰው ብርንና መዳብን፣ ብረትንና እርሳስን እንዲሁም ቈርቈሮን ለማቅለጥ በከውር ውስጥ አስገብቶ እሳት እንደሚያነድድበት፣ እኔም እንደዚሁ በቍጣዬና በመዓቴ ወደ ከተማዪቱ እሰበስባችኋለሁ፤ በዚያም አቀልጣችኋለሁ። 21ሰብስቤአችሁ የቍጣዬን እሳት በእስትንፋሴ አነድድባችኋለሁ፤ እናንተም በዚያ ውስጥ ቀልጣችሁ ትቀራላችሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ቍጣዬን በላያችሁ እንዳፈሰስሁ ታውቃላችሁ። 22ብር በከውር ውስጥ እንደሚቀልጥ፣ እናንተም በከተማዋ ውስጥ ትቀልጣላችሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር ቍጣዬን በላያችሁ እንዳፈሰስሁ ታውቃላችሁ።’ ”
23 የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 24“የሰው ልጅ ሆይ፤ ምድሪቱን፣ ‘አንቺ ያልነጻሽ በቍጣም ቀን ዝናብ ያላገኘሽ#22፥24 ከሰብዐ ሊቃናት ጋር ተመሳሳይ ሲሆን ዕብራይስጡ ግን ያልነጻሽ ወይም ያልዘነበብሽ ይለዋል። ምድር ነሽ’ በላት። 25መሳፍንቷ#22፥25 ከሰብዐ ሊቃናት ጋር ተመሳሳይ ሲሆን ዕብራይስጡ ግን ነቢያት ይለዋል እያገሣ ግዳዩን እንደሚቦጫጭቅ አንበሳ በውስጧ ያሤራሉ፤ ሕዝቡን ይበላሉ፤ ንብረትንና የከበሩ ነገሮችን ይነጥቃሉ፤ ብዙዎችንም ሴቶች መበለት ያደርጋሉ። 26ካህናቷ በሕጌ ላይ ያምፃሉ፤ ንዋያተ ቅድሳቴን ያረክሳሉ፤ የተቀደሰውን ከረከሰው አይለዩም፤ በጐደፈውና በንጹሑ መካከል ልዩነት እንደሌለ ያስተምራሉ፤ ሰንበታቴን ከማክበር ዘወር ብለዋል፤ በዚህም በመካከላቸው ተንቄአለሁ። 27በውስጧ የሚገኙ መኳንንቷ ግዳይ እንደሚቦጫጭቁ ተኵላዎች ናቸው፤ በግፍ ትርፍ ለመሰብሰብ ደም ያፈስሳሉ፤ ሕይወትም ያጠፋሉ። 28ነቢያቷም በሐሰት ራእይና በውሸት ሟርት ይህን ሁሉ ድርጊት ያድበሰብሱላቸዋል፤ እግዚአብሔርም ሳይናገር፣ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ ይላሉ። 29በምድሪቱ የሚኖረው ሕዝብ ይቀማል፤ ይዘርፋል፤ ፍትሕ በማጕደልም ድኻውንና ችግረኛውን ይጨቍናል፤ መጻተኛውንም ይበድላል።
30“ምድሪቱን እንዳላጠፋት ቅጥሩን የሚጠግን፣ በፈረሰውም በኩል በፊቴ የሚቆምላት ሰው ከመካከላቸው ፈለግሁ፤ ነገር ግን አንድም አላገኘሁም። 31ስለዚህ መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ፤ በጽኑ ቍጣዬም አነድዳቸዋለሁ፤ ያደረጉትንም በራሳቸው ላይ እመልሳለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”

Currently Selected:

ሕዝቅኤል 22: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ