ዘፀአት 7
7
1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ልብ በል፤ እኔ አንተን ለፈርዖን እንደ አምላክ (ኤሎሂም) አድርጌሃለሁ፤ ወንድምህ አሮንም ያንተ ነቢይ ይሆናል። 2እኔ የማዝህን ሁሉ ትናገራለህ፤ ወንድምህ አሮንም እስራኤላውያንን ከአገሩ እንዲወጡ ይለቅቃቸው ዘንድ ለፈርዖን ይነግረዋል። 3እኔ ግን የፈርዖንን ልብ አደነድናለሁ፤ ታምራዊ ምልክቶችንና ድንቆችን በግብፅ ላይ በብዛት ባደርግም እንኳ፣ አይሰማችሁም። 4ከዚያም እጄን በግብፅ ላይ አደርጋለሁ፤ በኀያል ፍርድም ሰራዊቴን፣ ሕዝቤን እስራኤላውያንን አወጣለሁ። 5እጄን በግብፅ ላይ ስዘረጋና እስራኤላውያንንም ከዚያ ሳወጣ፣ ግብፃውያን እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) መሆኔን ያውቃሉ።”
6ሙሴና አሮን እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ አዘዛቸው አደረጉ። 7ፈርዖንን ባነጋገሩበት ጊዜ ሙሴ ዕድሜው ሰማንያ ዓመት፣ አሮን ደግሞ ሰማንያ ሦስት ነበር።
የአሮን በትር እባብ ሆነች
8 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፣ 9“ፈርዖን፣ ‘ታምር አሳዩኝ’ ባላችሁ ጊዜ፣ አሮንን እንዲህ በለው፤ ‘በትርህን ውሰድና በፈርዖን ፊት ጣላት፤’ ከዚያም እባብ ትሆናለች።”
10ስለዚህ ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዛቸው አደረጉ። አሮን በትሩን በፈርዖንና በሹማምቱ ፊት ጣላት፤ እባብም ሆነች። 11ከዚያም ፈርዖን ጠቢባኑንና መተተኞቹን ጠራ፤ የግብፅ አስማተኞችም በድብቅ ጥበባቸው ያንኑ አደረጉ፤ 12እያንዳንዱ የያዛትን በትር ጣለ፤ እባብም ሆነች። ነገር ግን የአሮን በትር የእነርሱን በትሮች ዋጠች። 13ሆኖም የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ተናግሮ እንደ ነበረውም አላዳመጣቸውም።
የደም መቅሠፍት
14ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ ሕዝቡን ለመልቀቅ አልፈቀደም። 15ወደ ውሃው በሚሄድበት ጊዜ ማልደህ ወደ ፈርዖን ሂድ፤ እንድታገኘውም በአባይ ዳር ተጠባበቅ፤ ወደ እባብ ተለውጣ የነበረችውንም በትር በእጅህ ያዝ። 16ከዚያም እንዲህ በለው፤ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) “ሕዝቤ በምድረ በዳ ያመልኩኝ ዘንድ እንዲሄዱ ልቀቃቸው” ብዬ እንድነግርህ ላከኝ፤ አንተ ግን እስካሁን ድረስ እሺ አላልህም። 17እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለው ይህ ነው፤ “እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ሆንሁ በዚህ ታውቃለህ፤ እይ በዚህች በእጄ በያዝኋት በትር የአባይን ውሃ እመታለሁ፤ ወደ ደምም ይለወጣል። 18በአባይ ወንዝ ውስጥ ያለው ዓሣ ይሞታል፤ ወንዙ ይከረፋል፤ ግብፃውያንም ውሃውን መጠጣት አይችሉም።” ’ ”
19 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ “አሮንን፣ ‘በትርህን ውሰድና በግብፅ ውሆች ላይ፣ ይኸውም በምንጮች፣ በቦዮች፣ በኵሬዎችና በውሃ ማጠራቀሚያዎች ላይ እጅህን ዘርጋ’ ብለህ ንገረው፤ ወደ ደምም ይለወጣሉ። ከዕንጨትና ከድንጋይ በተሠሩ ውሃ መያዣዎች ውስጥም ሳይቀር በግብፅ ምድር ደም በየቦታው ይሆናል።”
20ሙሴና አሮን እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ አዘዛቸው አደረጉ። እርሱም በንጉሡና በሹማምንቱ ፊት በትሩን አንሥቶ የአባይን ወንዝ ውሃ መታ፤ ውሃውም በሙሉ ወደ ደም ተለወጠ። 21በአባይ ያሉት ዓሦች ሞቱ፤ ወንዙም ከመከርፋቱ የተነሣ ግብፃውያኑ ውሃውን ሊጠጡት አልቻሉም። በግብፅ ምድር ሁሉ ደም ነበረ።
22የግብፅ አስማተኞች በድብቅ ጥበባቸው ተመሳሳይ ነገር አደረጉ፤ የፈርዖንም ልብ ደነደነ፤ ልክ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ተናገረው ሙሴንና አሮንን አልሰማቸውም። 23ተመልሶ ወደ ቤተ መንግሥቱ ገባ እንጂ ይህን ከቁም ነገር አልቈጠረውም። 24ግብፃውያን ሁሉ የወንዙን ውሃ መጠጣት ባለመቻላቸው ውሃ ለማግኘት የአባይን ዳር ይዘው ጕድጓድ ቈፈሩ።
25 እግዚአብሔር (ያህዌ) አባይን ከመታ ሰባት ቀን ዐለፈ።
Currently Selected:
ዘፀአት 7: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.