የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፀአት 4:1-13

ዘፀአት 4:1-13 NASV

ሙሴም “ባያምኑኝስ፤ ቃሌን ባይቀበሉስ፤ ‘እግዚአብሔር አልተገለጠልህም’ ቢሉኝስ?” ብሎ መለሰ። እግዚአብሔርም፣ “በእጅህ የያዝሃት እርሷ ምንድን ናት?” ሲል ጠየቀው። እርሱም መልሶ፣ “በትር ናት” አለው። እግዚአብሔርም፣ “መሬት ላይ ጣላት” አለው። ሙሴ በትሩን መሬት ላይ ጣላት፤ እባብም ሆነች፤ ከአጠገቧም ሸሸ። እግዚአብሔር ሙሴን፣ “በል እጅህን ዘርጋና ጅራቷን ያዛት” አለው። ሙሴም እጁን ዘርግቶ ሲይዛት እባቧ ተለውጣ በእጁ ላይ እንደ ገና በትር ሆነች። እግዚአብሔርም “ይህ የሆነው የአባቶቻቸው አምላክ፣ የአብርሃም አምላክ፣ የይሥሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር የተገለጠልህ መሆኑን እንዲያምኑ ነው” አለው። እግዚአብሔርም ደግሞ፣ “እጅህን ብብትህ ውስጥ አስገባ” አለው። ሙሴም እጁን ብብቱ ውስጥ አስገባ፤ ከብብቱ ውስጥ ባወጣት ጊዜ እጁ እንደ በረዶ ለምጽ ሆነች። “አሁንም ደግሞ እጅህን ወደ ብብትህ መልሰህ አስገባ” አለው። ሙሴም እጁን መልሶ ብብቱ ውስጥ አስገባ፤ እንደ ገና እጁን ከብብቱ ውስጥ ባወጣት ጊዜ፣ ተመልሳ እንደ ሌላው የሰውነቱ ክፍል ሆነች። እግዚአብሔርም፣ “እንግዲህ ባያምኑህ ወይም የመጀመሪያውን ታምራዊ ምልክት ባይቀበሉ እንኳ ሁለተኛውን ያምናሉ። እነዚህን ሁለት ምልክቶች ባያምኑ ወይም ቃልህን ባይቀበሉ ግን፣ ከአባይ ወንዝ ጥቂት ውሃ ቀድተህ በደረቅ ምድር ላይ አፍስሰው። ከወንዙም ቀድተህ ያፈሰስኸው ውሃ በምድር ላይ ደም ይሆናል።” ሙሴም እግዚአብሔርን፣ “ጌታ ሆይ፤ ቀድሞም ሆነ፣ አንተ ከባሪያህ ጋራ ከተነጋገርህ ወዲህ፣ ከቶ አንደበተ ርቱዕ ሰው አይደለሁም። እኔ ኰልታፋና ንግግር የማልችል ሰው ነኝ” አለው። እግዚአብሔርም ሙሴን፣ “ለሰው አንደበቱን የሰጠው ማነው? ሰውን ደንቈሮ ወይም ዲዳ የሚያደርገው ማነው? ዐይን የሚሰጥ ወይም ዕውር የሚያደርገውስ ማነው? እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? በል አሁን ሂድ፤ እኔ እንድትናገር አደርግሃለሁ፤ የምትናገረውንም አስተምርሃለሁ” አለው። ሙሴ ግን፣ “ጌታ ሆይ፤ እባክህ ሌላ ሰው ላክ” አለው።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}