ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “አንተና ከግብጽ ያወጣኸው ሕዝብህ ይህን ስፍራ ለቅቃችሁ ‘ለዘርህ እሰጣለሁ’ በማለት ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅና ለያዕቆብ በመሐላ ተስፋ ወደ ገባሁላችሁ ምድር ሂዱ። መልአክን በፊትህ በመላክ፣ ከነዓናውያንን፣ አሞራውያንን፣ ኬጢያውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ኤዊያዊያንንና ኢያቡሳውያንን አስወጣለሁ። ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ምድር ውጡ፤ ነገር ግን ዐንገተ ደንዳና ሕዝብ ስለ ሆናችሁ፣ በመንገድ ላይ እንዳላጠፋችሁ እኔ ከእናንተ ጋራ አልሄድም።” ሕዝቡም እነዚህን አሳዛኝ ቃላት በሰሙ ጊዜ ይተክዙ ጀመር፤ ማንም ሰው አንዳች ጌጥ አላደረገም። እግዚአብሔርም ሙሴን፣ “እስራኤላውያንን፣ ‘እናንተ ዐንገተ ደንዳና ሕዝብ ናችሁ፤ ለአንዳፍታ እንኳ ከእናንተ ጋራ ዐብሬአችሁ ብሄድ አጠፋችሁ ነበር፤ አሁንም ጌጣጌጦቻችሁን አውልቁ፤ እናንተን ምን ማድረግ እንዳለብኝ እወስናለሁ’ ብለህ ንገራቸው” አለው። ስለዚህ እስራኤላውያን በኮሬብ ተራራ ላይ ጌጣጌጦቻቸውን አወለቁ። ሙሴ “የመገናኛው ድንኳን” ብሎ የጠራውን በመውሰድ፣ ከሰፈሩ ውጭ ራቅ ባለ ቦታ ላይ ይተክለው ነበር። እግዚአብሔርን መጠየቅ የሚፈልግ ሁሉ ከሰፈሩ ውጭ ወዳለው ወደ መገናኛው ድንኳን ይሄድ ነበር። ሙሴ ወደ ድንኳኑ በወጣ ጊዜ ሕዝቡ በመነሣት ወደ ድንኳኑ እስኪገባ ድረስ በየድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ ቆመው ይጠባበቁ ነበር። ሙሴ ወደ ድንኳኑ ገብቶ እግዚአብሔር ከሙሴ ጋራ እየተነጋገረ ሳለ የደመናው ዐምድ ወርዶ በመግቢያው ላይ ይቆም ነበር። ሕዝቡ የደመናውን ዐምድ በድንኳኑ ደጃፍ ላይ ቆሞ ሲያዩት ሁሉም በየድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ ቆመው ይሰግዱ ነበር። ሰው ከባልንጀራው ጋራ እንደሚነጋገር እግዚአብሔር ከሙሴ ጋራ ፊት ለፊት ይነጋገር ነበር፤ ከዚያም ሙሴ ወደ ሰፈሩ ይመለሳል፤ ረዳቱ የነበረው ብላቴናው የነዌ ልጅ ኢያሱ ግን ከድንኳኑ አይለይም ነበር። ሙሴ እግዚአብሔርን አለው፤ “ ‘እነዚህን ሕዝብ ምራ’ ብለህ ነግረኸኝ ነበር፤ ከእኔ ጋራ የምትልከው ማን እንደ ሆነ ግን አላሳወቅኸኝም፤ ‘አንተን በስም ዐውቅሃለሁ፤ በፊቴም ሞገስ አግኝተሃል’ ብለህ ነበር። በእኔ ደስ ተሠኝተህ ከሆነ፣ አንተን ዐውቅህና ያለ ማቋረጥ በፊትህ ሞገስ አገኝ ዘንድ መንገድህን አስተምረኝ፤ ይህ ሕዝብ የአንተ ሕዝብ መሆኑን አስታውስ።” እግዚአብሔር “ሀልዎቴ ከአንተ ጋራ ይሄዳል፤ ዕረፍትም እሰጥሃለሁ” ብሎ መለሰ። ከዚያም ሙሴ እንዲህ አለው፤ “ሀልዎትህ ከእኛ ጋራ ካልሄደ ከዚህ አትስደደን። አንተ ከእኛ ጋራ ካልሄድህ፣ አንተ በእኔና በሕዝብህ መደሰትህን ሌላው እንዴት ያውቃል? እኔንና ሕዝብህንስ በገጸ ምድር ከሚገኙት ከሌሎቹ ሕዝቦች ሁሉ ልዩ የሚያደርገን ሌላ ምን አለ?” እግዚአብሔርም ሙሴን፣ “በአንተ ደስ ስላለኝና በስም ስለማውቅህ፣ የጠየቅኸውን ያንኑ አደርጋለሁ” አለው። ከዚያም ሙሴ “እባክህ፤ ክብርህን አሳየኝ” አለው። እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “መልካምነቴ ሁሉ በፊትህ እንዲያልፍ አደርጋለሁ፤ በፊትህም ስሜን እግዚአብሔርን ዐውጃለሁ፤ የምምረውን እምረዋለሁ፤ የምራራለትንም ራራለታለሁ፤ ነገር ግን፣ ማንም እኔን አይቶ መኖር ስለማይችል፣ ፊቴን ማየት አትችልም።” ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “በአጠገቤ ስፍራ አለ፤ አንተም በዐለት ላይ ትቆማለህ፤ ክብሬ በዚያ ሲያልፍ በዐለቱ ስንጥቅ ውስጥ አደርግሃለሁ፤ በዚያም እስከማልፍ ድረስ በእጄ እጋርድሃለሁ፤ ከዚያም እጄን አነሣለሁ፤ ጀርባዬንም ታያለህ፤ ፊቴ ግን መታየት የለበትም።”
ዘፀአት 33 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፀአት 33
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፀአት 33:1-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች