ዘፀአት 31
31
ባስልኤልና ኤልያብ
31፥2-6 ተጓ ምብ – ዘፀ 35፥30-35
1ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“እነሆ፤ ከይሁዳ ነገድ የሑር የልጅ ልጅ የሆነውን የኡሪን ልጅ ባስልኤልን መርጬዋለሁ። 3በጥበብ፣ በብልኀት፣ ዕውቀትና ማንኛውንም ዐይነት ሙያ እንዲኖረው የእግዚአብሔርን መንፈስ ሞልቼዋለሁ። 4ይኸውም በወርቅ፣ በብርና በንሓስ ለሚሠሩት ሥራዎች በጥበብ የተሠሩ ጌጦችን እንዲያበጅ፣ 5ድንጋዮችን እንዲቈፍርና እንዲጠርብ ከዕንጨትም ጥርብ እንዲያወጣ፣ ሁሉንም ዐይነት የእጅ ጥበብ ሥራዎችን እንዲያከናውን ነው። 6በተጨማሪም ከዳን ነገድ የሆነውን የአሂሳሚክን ልጅ ኤልያብን እንዲረዳው መርጬዋለሁ።
“እንዲሁም ያዘዝሁህን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ ለእጅ ጥበብ ዐዋቂዎች ሁሉ ብልኀትን ሰጥቻቸዋለሁ፤
7“ይኸውም የመገናኛውን ድንኳን፣
የምስክሩን ታቦት በላዩ ላይ ካለው ከስርየት መክደኛው ጋራ፣
ሌሎች የድንኳኑን መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ፣
8ጠረጴዛውን ከነዕቃዎቹ፣
ከንጹሕ ወርቅ የተሠራውን የወርቅ መቅረዝ ከነዕቃዎቹ፣
የዕጣኑን መሠዊያ፣
9የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውን ከነዕቃዎቹ፣
ሰኑን፣ ከነማስቀመጫው፣
10ከፈትል የተሠሩ ልብሶችን
ይኸውም የካህኑን የአሮንን የተቀደሱ ልብሶችንና
ካህናት ሆነው ሲያገለግሉ የሚለብሷቸውን የወንድ ልጆቹ ልብሶች፣
11እንዲሁም የመቅደሱ የሆነውን ቅብዐ ዘይትና ጣፋጭ ሽታ ያለውን ዕጣን እንዲሠሩ ነው።
“ልክ እኔ እንዳዘዝሁህ ያብጇቸው።”
ሰንበት
12ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 13“ለእስራኤላውያን ንገራቸው፤ ‘ሰንበቴን ማክበር አለባችሁ፤ ይህም በእኔና በእናንተ መካከል በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ምልክት ይሆናል፤ ይኸውም የምቀድሳችሁ#31፥13 ወይም፣ ቅዱስ አድርጌ የምለያችሁ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ እንድታውቁ ነው።
14“ ‘ለእናንተ ቅዱስ ነውና ሰንበትን አክብሩ፤ ማንም ቢያረክሰው በሞት ይቀጣል፤ በዚያ ቀን ማንም የሚሠራ ቢኖር ከወገኑ ተነጥሎ ይለይ። 15ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ የዕረፍት ሰንበት ነው፤ በሰንበት ቀን ማንም ቢሠራ በሞት መቀጣት አለበት። 16እስራኤላውያን በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ሰንበትን በመጠበቅ የዘላለም ኪዳን አድርገው ማክበር አለባቸው፤ 17በእኔና በእስራኤላውያን መካከል ለዘላለም ምልክት ይሆናል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን በስድስት ቀን ሠርቶ፣ በሰባተኛው ቀን ከሥራ ታቅቦ ዐርፏልና።’ ”
18 እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ለሙሴ መናገሩን ከፈጸመ በኋላ፣ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን የድንጋይ ጽላት፣ ሁለቱን የምስክር ጽላት ለርሱ ሰጠው።
Currently Selected:
ዘፀአት 31: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.