የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፀአት 29

29
የካህናት መቀደስ
29፥1-37 ተጓ ምብ – ዘሌ 8፥1-36
1“ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉኝ ትቀድሳቸው ዘንድ የምታደርገው ይህ ነው፤ ነቀፋ የሌለባቸው አንድ ወይፈንና ሁለት አውራ በጎች ውሰድ። 2እርሾ ከሌለው ከምርጥ የስንዴ ዱቄት ቂጣ፣ በዘይት የተለወሰ የቂጣ ዕንጐቻና በዘይት የተቀባ ኅብስት ጋግር። 3በሌማት ላይ አድርገህ ከወይፈኑና ከሁለቱ አውራ በጎች ጋራ አቅርባቸው። 4ከዚያም አሮንና ወንድ ልጆቹን ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በማምጣት በውሃ ዕጠባቸው። 5ልብሶቹን ወስደህ ለአሮን አልብሰው፤ እጀ ጠባብ፣ የኤፉድ ቀሚስ፣ ኤፉዱንና የደረት ኪሱን አልብሰው፤ ኤፉዱን በርሱ ላይ በጥበብ በተሠራ መታጠቂያ እሰረው። 6መጠምጠሚያውን በራሱ ላይ በማድረግ የተቀደሰውን አክሊል ከመጠምጠሚያው ጋራ አያይዘው። 7ቅብዐ ዘይት ወስደህ በራሱ ላይ በማፍሰስ ቅባው። 8ወንዶች ልጆቹን አምጥተህ እጀ ጠባቦቹን አልብሳቸው። 9የራስ ማሰሪያዎችንም አድርግላቸው#29፥9 ዕብራይስጡ፣ የሰላም መሥዋዕት አድርግላቸው ይላል።፤ ከዚያም አሮንንና ወንዶች ልጆቹን መታጠቂያዎችን አስታጥቃቸው፤ ክህነት የዘላለም ሥርዐት ይሆንላቸዋል።
“በዚህም መንገድ አሮንንና ወንዶች ልጆቹን ትክናቸዋለህ።
10“ወይፈኑን በመገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት በማምጣት አሮንና ወንዶች ልጆቹ በራሱ ላይ እጆቻቸውን ይጫኑበት። 11በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ወይፈኑን ዕረደው። 12ከወይፈኑ ደም ወስደህ የመሠዊያው ቀንዶች ላይ በጣቶችህ አድርግበት፤ የቀረውንም ከመሠዊያው ሥር አፍስሰው። 13ከዚያም በሆድ ዕቃዎች ያለውን ስብ ሁሉ፣ የጕበቱን መሸፈኛና ሁለቱንም ኵላሊቶች በዙሪያቸው ካለው ስብ ጋራ ወስደህ በመሠዊያው ላይ አቃጥላቸው። 14ነገር ግን የወይፈኑን ሥጋ፣ ቈዳውንና ፈርሱን ከሰፈር ውጭ አቃጥለው፤ የኀጢአት መሥዋዕት ነው።
15“ከሁለቱ አውራ በጎች አንዱን ወስደህ፣ አሮንና ወንዶች ልጆቹ በራሱ ላይ እጃቸውን ይጭኑበታል። 16አውራውንም በግ ዕረደው፤ ደሙንም ወስደህ በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ርጨው። 17አውራ በጉን በየብልቱ ቈራርጠህ፣ የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን ዐጥበህ ከራሱና ከሌሎቹ ቍርጥራጭ ብልቶች ጋራ አኑረው። 18ከዚያም አውራ በጉን በሙሉ በመሠዊያው ላይ አቃጥለው፤ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ጣፋጭ መዐዛና ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት ነው።
19“ሌላውን አውራ በግ ወስደህ አሮንና ወንዶች ልጆቹ በራሱ ላይ እጆቻቸውን ይጭኑበታል። 20አውራውንም በግ ዕረደው፤ ከደሙም ወስደህ የአሮንንና የወንዶች ልጆቹን የቀኝ ጆሮዎቻቸውን ጫፍ የቀኝ እጆቻቸውን አውራ ጣቶች፣ የቀኝ እግራቸውንም አውራ ጣቶች ቅባቸው፤ ከዚያም ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ርጨው። 21በመሠዊያው ላይ ካለው ደምና ከቅብዐ ዘይቱ ወስደህ በአሮንና በልብሶቹ ላይ እንዲሁም በወንዶች ልጆቹና በልብሶቻቸው ላይ ርጨው። ከዚያም እርሱና ወንዶች ልጆቹ እንዲሁም ልብሶቻቸው የተቀደሱ ይሆናሉ።
22“ከዚህ አውራ በግ ሥቡን፣ ላቱን፣ በሆድ ዕቃው ውስጥ ያለውን ስብ፣ የጕበቱን ሽፋን፣ ሁለቱን ኵላሊቶችና በዙሪያቸው ያለውን ሥብና ቀኙን ወርች ውሰድ፤ ይህ የክህነት አውራ በግ ነው። 23እግዚአብሔር ፊት በሌማት ካለው ያለ እርሾ ከተጋገረው ቂጣ፣ ዳቦ፣ በዘይት የተሠራ ዕንጐቻና ኅብስት ውሰድ። 24እነዚህን ሁሉ በአሮንና በወንዶች ልጆቹ እጆች ላይ በማኖር እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት ወዝውዛቸው። 25ከዚያም ከእጃቸው ወስደህ ከሚቃጠለው መሥዋዕት ጋራ ለእግዚአብሔር መልካም መዐዛ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ አቃጥለው፤ ይህም ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት ነው። 26ለአሮን ክህነት የአውራ በጉን ፍርምባ ከወሰድህ በኋላ እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት ወዝውዘው፤ ይህም የአንተ ድርሻ ይሆናል።
27“ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ ለክህነት የሆኑትን የአውራውን በግ ብልቶች ቀድሳቸው። የተወዘወዘውን ፍርምባና የቀረበውን ወርች 28ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ የዘወትር የእስራኤላውያን ድርሻ የሚሆነው ይህ ነው፤ ከኅብረት መሥዋዕታቸው#29፥28 በትውፊት፣ የሰላም መሥዋዕት በመባል ይታወቃል። እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት ነው።
29“የአሮን የተቀደሱ ልብሶች ለትውልዶቹ ይሆናሉ፤ ይኸውም በእነርሱ ይቀቡና ክህነትን ይቀበሉ ዘንድ ነው። 30ካህን በመሆን እርሱን የሚተካውና በመቅደሱ ለማገልገል ወደ መገናኛው ድንኳን የሚመጣው ወንድ ልጅ ሰባት ቀን ይለብሳቸዋል።
31“የክህነቱን አውራ በግ ወስደህ ሥጋውን በተቀደሰ ስፍራ ቀቅለው። 32አሮንና ወንዶች ልጆቹ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ የአውራውን በግ ሥጋና በሌማት ያለውን ዳቦ ይብሉ። 33ለክህነታቸውና ለመቀደሳቸው ማስተስረያ የሆኑትን እነዚህን መሥዋዕቶች ይብሉ፤ የተቀደሱ ስለ ሆኑ ሌላ ማንም አይብላቸው። 34ከክህነቱ የአውራ በግ ሥጋ ወይም ከቂጣው እስከ ንጋት ድረስ ቢተርፍ አቃጥለው፤ የተቀደሰ ስለ ሆነ መበላት የለበትም።
35“ክህነታቸውን በሰባት ቀን በመፈጸም ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ ያዘዝሁህን ሁሉ አድርግላቸው። 36ለማስተስረያ የሚሆን አንድ ወይፈን የኀጢአት መሥዋዕት አድርገህ በየዕለቱ ሠዋ፤ ለመሠዊያውም ማስተስረያ በማቅረብ መሠዊያውን አንጻው፤ ትቀድሰውም ዘንድ ቅባው። 37ለሰባት ቀን ለመሠዊያው ማስተስረያ በማድረግ ቀድሰው፤ ከዚያም መሠዊያው እጅግ የተቀደሰ ይሆናል፤ የሚነካውም ሁሉ የተቀደሰ ይሆናል።
38“በየዕለቱ ያለ ማቋረጥ በመሠዊያው ላይ የምታቀርበው ይህ ነው፤ ዓመት የሞላቸው ሁለት የበግ ጠቦቶች፤ 39አንዱን ጠቦት በማለዳ፣ ሌላውን በማታ አቅርብ። 40ከመጀመሪያው የበግ ጠቦት ጋራ የኢፍ መስፈሪያ አንድ ዐሥረኛ#29፥40 ይህ ምናልባት 1.6 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ምርጥ ዱቄትን ተወቅጦ ከተጠለለ ሩብ ኢፍ#29፥40 ይህ ምናልባት 1 ሊትር ያህል ነው። ዘይት ጋራ ለውስና ሩብ ሂን ወይንን ደግሞ የመጠጥ መሥዋዕት በማድረግ አቅርብ። 41ሌላውን የበግ ጠቦት በማለዳው እንደ ቀረበው ተመሳሳይ ከሆነው የእህልና የመጠጥ መሥዋዕት ጋራ በማታ ሠዋው፤ ይህም ጣፋጭ መዐዛና ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት ነው።
42“ይህ የሚቃጠል መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ በሚመጡት ትውልዶች ዘወትር ይደረጋል፤ በዚያ እገናኝሃለሁ፤ እናገርሃለሁም፤ 43በዚያ ደግሞ ከእስራኤላውያን ጋራ እገናኛለሁ፤ ስፍራውም በክብሬ ይቀደሳል።
44“ስለዚህ የመገናኛው ድንኳንና መሠዊያውን እኔ እቀድሳለሁ፤ ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉኝ አሮንና ወንድ ልጆቹን እቀድሳለሁ። 45ከዚያም በእስራኤላውያን መካከል እኖራለሁ፤ አምላካቸውም እሆናለሁ። 46በመካከላቸውም እኖር ዘንድ ከግብጽ ያወጣኋቸው እኔ አምላካቸው እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ነኝ።

Currently Selected:

ዘፀአት 29: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ