ዘፀአት 28
28
ልብሰ ተክህኖ
1“ካህናት ሆነው ያገለግሉኝ ዘንድ ከእስራኤላውያን መካከል ወንድምህ አሮንን ከወንዶች ልጆቹ ከናዳብ፣ ከአብዩድ፣ ከአልዓዛርና ከኢታምር ጋር ወደ አንተ አቅርባቸው። 2ለእርሱም ማዕረግና ክብር ለመስጠት ለወንድምህ ለአሮን የተቀደሱ መጐናጸፊያዎችን አብጅለት። 3ካህን ሆኖ እንዲያገለግለኝ የተለየ ይሆን ዘንድ ጥበብ ለሰጠኋቸው በዚህ ጕዳይ ላይ ጥበበኛ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ ለአሮን መጐናጸፊያዎችን እንዲሠሩለት ንገራቸው። 4የሚሠሯቸው መጐናጸፊያዎች የደረት ልብስ ኤፉድ ቀሚስ፣ ጥልፍ ሸሚዝ፣ ጥምጥምና መታጠቂያ ናቸው፤ ካህን ሆነው ያገለግሉኝ ዘንድ የተቀደሱ መጐናጸፊያዎችን ለአሮንና ለወንድ ልጆቹ ይሠራሉ። 5ወርቅ፣ ሰማያዊ፣ ሐምራዊ፣ ቀይ ማግና እንዲሁም ቀጭን በፍታ ይጠቀሙ።
ኤፉድ
28፥6-14 ተጓ ምብ – ዘፀ 39፥2-7
6“የጥልፍ ዐዋቂዎች ኤፉዱን ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ ይሥሩት። 7መተሳሰር እንዲችል ሆኖ፣ ዳርና ዳር ከሚገኙት ከሁለቱ ጐኖች ጋር የተያያዙ ሁለት የትከሻ ንጣዮች ይኑሩት። 8በጥበብ የተጠለፈው የወገብ መታጠቂያ ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ ሐር ከኤፉድ ጋር አንድ ወጥ ሆኖ የተሠራ ይሁን።
9“ሁለት የመረግድ ድንጋዮች ውሰድና የእስራኤልን ልጆች ስሞቻቸውን ቅረጽባቸው። 10እንደ ልደታቸው ቅደም ተከተል ስድስቱን ስሞች በአንዱ ድንጋይ ላይ የቀሩትንም ስሞች በሌላው ላይ ቅረጽባቸው። 11የቅርጽ ሠራተኛ ማኅተም እንደሚቀርጽ የእስራኤልን ልጆች ስም በሁለቱ ድንጋዮች ላይ ቅረጽ፤ ከዚያም ድንጋዮቹን በወርቅ ፈርጥ ክፈፋቸው፤ 12ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ ድንጋዮች ይሆኑ ዘንድ በኤፉዱ ትከሻ ላይ ካሉት ንጣዮች ጋር አያይዛቸው፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት መታሰቢያ እንዲሆኑ አሮን ስሞቹን በትከሻው ላይ ይሸከማቸው። 13የወርቅ ፈርጦችን አብጅ፤ 14እንደ ገመድ ያሉ ሁለት በንጹሕ ወርቅ የተጐነጐኑ ድሪዎችን አብጅተህ ከፈርጡ ጋር አያይዛቸው።
የደረት ኪስ
28፥15-28 ተጓ ምብ – ዘፀ 39፥8-21
15“የፍርድ መስጫውን የደረት ኪስ ብልኅ ሠራተኛ እንደሚሠራው አድርገህ አብጀው፤ ልክ እንደ ኤፉዱ ከወርቅ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ አብጀው። 16ርዝመቱ አንድ ስንዝር፣ ስፋቱ አንድ ስንዝር#28፥16 ወደ 22 ሴንቲ ሜትር ያህል ነው። ሆኖ ባለ አራት ማእዘንና በድርቡ የታጠፈ ይሁን። 17ከዚያም በላዩ ላይ በአራት ረድፍ የከበሩ ድንጋዮች አድርግበት፤ በመጀመሪያው ረድፍ ሰርዲዮን፣ ቶጳዝዮን፣ የሚያበረቀርቅ ዕንቍ፤ 18በሁለተኛውም ረድፍ በሉር፣ ሰንፔር#28፥18 ወይም፣ ላፒስ ላዙሊ፣ አልማዝ፤ 19በሦስተኛው ረድፍ ያክንት፣ ኬልቄዶን፣ አሜቴስጢኖስ፤ 20በአራተኛውም ረድፍ ቢረሌ፣ መረግድና ኢያስጲድ#28፥20 የእነዚህ የከበሩ ማዕድኖች ትክክለኛ ማንነት በትክክል አይታወቅም። አድርግበት፤ በወርቅ ፈርጥም ክፈፋቸው። 21የዐሥራ ሁለቱ ነገዶች ስሞች እንደ ማኅተም የተቀረጸባቸው ለእያንዳንዱ የእስራኤል ልጆች ስም ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች ይሁኑ።
22“ለደረት ኪሱ ከንጹሕ ወርቅ እንደ ገመድ ሆኖ የተጌጠ ጕንጕን አብጅለት። 23ለእርሱም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች አብጅተህ ከደረት ኪሱ ሁለት ጐኖች ጋር አያይዘው። 24ሁለቱን የወርቅ ጕንጕኖች በደረት ኪሱ ጐኖች ላይ ካሉት ቀለበቶች ጋር አያይዛቸው። 25ሌሎቹን የጕንጕን ጫፎች በፊት ላይ ካለው ኤፉድ በትከሻው ላይ ካሉት ንጣዮች ጋር በማጋጠም ከሁለቱ የወርቅ ፈርጦች ጋር አያይዛቸው። 26ሁለት የወርቅ ቀለበቶች አበጅተህ ከኤፉዱ ቀጥሎ ባለው በውስጠኛ ጠርዝ ላይ፣ በሌላ በኩል ካሉት ሁለት የደረት ኪስ ጐኖች ጋር አያይዛቸው። 27ሁለት ተጨማሪ የወርቅ ቀለበቶች አበጅተህ ከኤፉዱ መታጠቂያ ከፍ ብሎ ከመጋጠሚያው አጠገብ ካለው በኤፉዱ ፊት ለፊት፣ በትከሻ ላይ ካሉት ንጣዮች ግርጌ ጋር አያይዘው። 28የደረት ኪሱም ቀለበቶች፣ የደረት ኪሱ ከኤፉዱ ጋር እንዳይላቀቅ፣ ከመታጠቂያው ጋር በማገናኘት በሰማያዊ ገመድ ከኤፉዱ ቀለበቶች ጋር ይያያዙ።
29“አሮን ወደ መቅደሱ በሚገባበት ጊዜ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ለዘላለም መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የእስራኤልን ልጆች ስሞች በፍርድ መስጫው ደረት ኪስ በልቡ ላይ ይሸከም። 30ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት በሚገባበት ጊዜ በአሮን ልብ ላይ ይሆኑ ዘንድ ኡሪሙንና ቱሚሙን በደረት ኪሱ አድርግ፤ ስለዚህ አሮን ሁልጊዜ ለእስራኤላውያን የፍርድ መስጫውን በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት በልቡ ላይ ይሸከማል።
ሌሎቹ አልባሳት
28፥31-43 ተጓ ምብ – ዘፀ 39፥22-31
31“የኤፉዱ ቀሚስ ሙሉ በሙሉ ከሰማያዊ ጨርቅ ይሁን፤ 32ከላይ በኩል በመካከሉ ዐንገትጌ አድርገህ አብጀው፤ እንዳይቀደድም በማስገቢያው ዙሪያ እንደ ክሳድ ያለ ዝምዝም ጠርዝ#28፥32 በዕብራይስጡ የዚህ ቃል ትክክለኛ ፍችው አይታወቅም። ሥራለት። 33በጨርቁ ጠርዝ ዙሪያ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ ሮማኖቹን፣ በመካከሉም የወርቅ ሻኵራዎችን አብጅ። 34የወርቅ ሻኵራዎቹና ሮማኖቹ በጨርቁ ጠርዝ ዙሪያ በመፈራረቅ ይሆናሉ። 35አሮንም በአገልግሎቱ ጊዜ ይህን መልበስ አለበት፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ወደ መቅደሱ በገባና ከመቅደሱ ሲወጣ እንዳይሞት የሻኵራዎቹ ድምፅ ይሰማል።
36“ከንጹሕ ወርቅ ዝርግ ሳሕን አበጅተህ፣ ‘ቅዱስ እግዚአብሔር (ያህዌ)’ በማለት በማኅተም ላይ እንደሚቀረጽ ቅረጸው። 37ከመጠምጠሚያው ጋር እንዲያያዝ ሰማያዊ ፈትል እሰርበት፤ እርሱም በመጠምጠሚያው ፊት በኩል ይሁን። 38ይህም በአሮን ግንባር ላይ ይሆናል፤ እስራኤላውያን ለይተው በሚያቀርቧቸው በማናቸውም የተቀደሱ ስጦታዎች ውስጥ ያለውን በደል ይሸከማል፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ተቀባይነት እንዲኖራቸው ሁልጊዜ በአሮን ግንባር ላይ ይሆናል።
39“ሸሚዙን ከቀጭን በፍታ ሥራ፤ መጠምጠሚያውንም ከቀጭን በፍታ አብጀው፤ መታጠቂያውንም ጥልፍ ጠላፊ የሠራው ይሁን። 40የአሮን ወንድ ልጆች ክብርና ማዕረግ እንዲኖራቸው ሸሚዞችን፣ መታጠቂያዎችን፣ የራስ ማሰሪያዎችን አብጅላቸው። 41እነዚህን ልብሶች ለአሮንና ለወንድ ልጆቹ ካለበስህ በኋላ ቅባቸው፤ ካናቸው፤ ካህናት ሆነው ያገለግሉኝም ዘንድ ቀድሳቸው።
42“ከወገብ ጀምሮ እስከ ጭን የሚደርስ ሰውነትን የሚሸፍን ከበፍታ የተሠራ የውስጥ ቍምጣ አብጅ። 43አሮንና ወንድ ልጆቹ ወደ መገናኛው ድንኳን በሚገቡበት ጊዜ ወይም በመቅደሱ ለማገልገል ወደ መሠዊያው ሲቀርቡ፣ በደል ፈጽመው እንዳይሞቱ እነዚህን መልበስ አለባቸው።
“ለአሮንና ለትውልዶቹ ይህ የዘላለም ሥርዐት ይሆናል።
Currently Selected:
ዘፀአት 28: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.