በዚያች ምሽት ድርጭቶች መጥተው ሰፈሩን አለበሱት፤ በነጋውም በሰፈሩ ዙሪያ ጤዛ ተኝቶበት ነበር። ጤዛው ከረገፈ በኋላ በሜዳው ላይ ስስ የሆነ ዐመዳይ የሚመስል የተጋገረ ነገር በምድረ በዳው ላይ ታየ። እስራኤላውያንም ይህን ባዩ ጊዜ ምን እንደ ሆነ ባለማወቃቸው እርስ በርሳቸው፣ “ይህ ነገር ምንድን ነው?” ተባባሉ። ሙሴም፣ “ይህ ትበሉት ዘንድ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሰጣችሁ እንጀራ ነው አላቸው። እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘው ይህ ነው፤ ‘እያንዳንዱ የሚያስፈልገውን ያህል ይሰብስብ፤ በድንኳናችሁ ባለው ሰው ልክ ለእያንዳንዱ አንድ ጎሞር ውሰዱ’ ” ብሎ እግዚአብሔር (ያህዌ) አዝዟል። እስራኤላውያንም እንደ ተነገራቸው አደረጉ፤ አንዳንዶች አብዝተው፣ አንዳንዶች ደግሞ አሳንሰው ሰበሰቡ። የሰበሰቡትን በጎሞር በሰፈሩ ጊዜ ብዙ የሰበሰበው አልተረፈውም፤ ጥቂት የሰበሰበውም አልጐደለበትም፤ እያንዳንዱ የሰበሰበው የሚያስፈልገውን ያህል ሆነ። ሙሴም፣ “ማንም ከዚህ ለነገ ምንም ማስተረፍ የለበትም” አላቸው። ሆኖም ግን አንዳንዶቹ ሙሴ የተናገረውን ቸል በማለት ከሰበሰቡት ውስጥ ከፊሉን አስተርፈው አሳደሩ፤ በማግስቱም ጧት ተልቶ መሽተት ጀመረ፤ ስለዚህ ሙሴ ተቈጣቸው። በየማለዳው እያንዳንዱ የሚያስፈልገውን ያህል ሰበሰበ፤ ፀሓዩ እየበረታ በሄደም ጊዜ ቀለጠ። በስድስተኛው ቀን ለእያንዳንዱ ሰው ሁለት ሁለት ጎሞር አድርገው ዕጥፍ ሰበሰቡ፤ የማኅበሩም አለቆች ወደ ሙሴ መጥተው ይህንኑ ነገሩት። እርሱም አላቸው፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘው ይህ ነው፤ ‘ነገ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተቀደሰ ሰንበት በመሆን፣ የዕረፍት ቀን ይሆናል።’ ስለዚህ መጋገር የምትፈልጉትን ጋግሩ፤ መቀቀል የምትፈልጉትን ቀቅሉ። የተረፈውን አስቀምጡ፤ እስከ ጧትም ድረስ አቈዩት።” ስለዚህ ሙሴ እንዳዘዘው እስከ ጧት ድረስ አቈዩት፤ አልሸተተም፤ ወይም አልተላም። ሙሴም እንዲህ አለ፤ “ዛሬውኑ ብሉት፤ ዛሬ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰንበት ነውና። ዛሬ በመሬት ላይ ምንም አታገኙም። ስድስት ቀን ትሰበስቡታላችሁ፤ በሰባተኛው ቀን በሰንበት ዕለት ግን ምንም ነገር አይኖርም።” ሆኖም አንዳንዶቹ በሰባተኛው ቀን ለመሰብሰብ ወጡ፤ ነገር ግን ምንም አላገኙም። ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ “ትእዛዞቼንና መመሪያዎቼን ለመፈጸም እስከ መቼ እንቢ ትላላችሁ? እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰንበትን የሰጣችሁ መሆኑን ልብ በሉ፤ በስድስተኛው ቀን ለሁለት ቀን የሚሆን እንጀራ የሰጣችሁ ለዚህ ነው። በሰባተኛው ቀን እያንዳንዱ ሰው ባለበት ይቈይ፤ ማንም አይወጣም።” ስለዚህ ሕዝቡም በሰባተኛው ቀን ዐረፉ።
ዘፀአት 16 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፀአት 16
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፀአት 16:13-30
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos