ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ “እስራኤላውያን ተመልሰው በሚግዶልና በባሕሩ መካከል ባለው በፊሀሒሮት አጠገብ እንዲሰፍሩ ንገራቸው፤ በበኣልዛፎንም አንጻር በባሕሩ አጠገብ ይስፈሩ። ‘ፈርዖን እስራኤላውያን ግራ ተጋብተው በምድረ በዳ በመቅበዝበዝ ይንከራተታሉ’ ብሎ ያስባል። እኔም የፈርዖንን ልብ ስለማደነድነው ያሳድዳቸዋል፤ ነገር ግን በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ ለራሴ ክብርን አገኛለሁ፤ ግብፃውያንም እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) መሆኔን ያውቃሉ።” እስራኤላውያንም ይህንኑ አደረጉ። የግብፅ ንጉሥ ሕዝቡ መሄዳቸው በተነገረው ጊዜ፣ ፈርዖንና ሹማምቱ ስለ እነርሱ የነበራቸውን ሐሳብ በመለወጥ፣ “ምን ማድረጋችን ነው? እስራኤላውያን እንዲሄዱ ለቀቅናቸው፤ አገልግሎታቸውንም ዐጣን” አሉ። ስለዚህ ሠረገላው እንዲዘጋጅለት አደረገ፤ ሰራዊቱንም ይዞ ተንቀሳቀሰ። ስድስት መቶ ምርጥ ሠረገላዎችን ከሌሎች የግብፅ ሠረገላዎች ጋር ከነጦር አዛዦቻቸው አሰልፎ ተነሣ። እግዚአብሔር (ያህዌ) የንጉሡን የፈርዖንን ልብ ስለ አደነደነው በልበ ሙሉነት ከግብፅ የሚወጡትን እስራኤላውያን አሳደዳቸው። ግብፃውያን፣ ይኸውም የፈርዖን ፈረሶችና ሠረገላዎች፣ ፈረሰኞችና እግረኞች ሁሉ እስራኤላውያንን አሳደዷቸው፤ በበአልዛፎን አንጻር በባሕሩ አጠገብ በፊሀሒሮት ሰፍረው ሳሉ ደረሱባቸው። ፈርዖን በቀረበ ጊዜ እስራኤላውያን ቀና ብለው ተመለከቱ፤ እነሆ፣ ግብፃውያን ይከታተሏቸው ነበር፤ እነርሱም በታላቅ ፍርሀት ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጮኹ። እነርሱም ሙሴን እንዲህ አሉት፤ “በምድረ በዳ እንድንሞት ያመጣኸን በግብፅ መቃብር ቦታ ጠፍቶ ነውን? ከግብፅ አውጥተህ ምን አደረግህልን? በግብፅ ሳለን፣ ‘ተወን እባክህ፤ ግብፃውያንን እናገልግል’ አላልንህም ነበርን? በምድረ በዳ ከምንሞት ግብፃውያንን ብናገለግል ይሻል ነበር!” ሙሴም ለሕዝቡ መለሰላቸው፤ “አትሸበሩ፣ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ዛሬ የሚያደርግላችሁን መታደግ ታያላችሁ፤ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ዳግም አታዩአቸውም። እግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተ ያለባችሁ መታገሥ ብቻ ነው።” ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለምን ትጮኹብኛላችሁ? ይልቅስ እስራኤላውያንን ወደ ፊት እንዲጓዙ ንገራቸው፤ ውሃውን ለመክፈል በትርህን አንሣና እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ እስራኤላውያን በባሕሩ ውስጥ በየብስ ይሻገራሉ። ተከትለዋቸው እንዲገቡም የግብፃውያንን ልብ አጸናለሁ፤ በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ፣ በሠረገሎቹና በፈረሰኞቹ ለራሴ ክብርን አገኛለሁ። በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ በከበርሁ ጊዜ፣ ግብፃውያን እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” ከዚያም ከእስራኤል ሰራዊት ፊት ፊት ሆኖ ሲሄድ የነበረው የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መልአክ ተመለሰና ወደ ኋላቸው መጣ፤ የደመናውም ዐምድ እንዲሁ ከፊት ተነሥቶ ከኋላቸው ቆመ፤ በግብፅና በእስራኤል ሰራዊት መካከል በመሆን፣ ሌሊቱን ሙሉ ደመናው በአንድ በኩል ጨለማን ሲያመጣ፣ በሌላው በኩል ብርሃን አመጣ፤ ስለዚህ ሌሊቱን በሙሉ አንዱ ወደ ሌላው ሊጠጋ አልቻለም። ሙሴ እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሌሊቱን በሙሉ ብርቱ የምሥራቅ ነፋስ አስነሥቶ ባሕሩን ወደ ኋላ በማሸሽ ደረቅ ምድር አደረገው፤ ውሃውም ተከፈለ። እስራኤላውያን ውሃው በግራና በቀኝ እንደ ግድግዳ ሆኖ በየብስ በባሕሩ ውስጥ ዐለፉ።
ዘፀአት 14 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፀአት 14
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፀአት 14:1-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos