አስቴር 5
5
አስቴር ለንጉሡ ያቀረበችው ልመና
1በሦስተኛው ቀን አስቴር የክብር ልብሷን ለብሳ በንጉሡ አዳራሽ ፊት ለፊት ባለው በቤተ መንግሥቱ ውስጠኛ አደባባይ ገብታ ቆመች። ንጉሡም አዳራሹ ውስጥ በመግቢያው ትይዩ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ነበር። 2ንግሥት አስቴር በአደባባዩ ላይ ቆማ ሲያያት ደስ አለው፤ በእጁ የያዘውን የወርቅ ዘንግ ዘረጋላት፤ አስቴርም ቀረብ ብላ የዘንጉን ጫፍ ነካች።
3ከዚያም ንጉሡ፣ “ንግሥት አስቴር ሆይ፤ ለምን መጣሽ? ከእኔ የምትፈልጊውስ ምንድን ነው? እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ቢሆን ይሰጥሻል” አላት።
4አስቴርም መልሳ፣ “ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ቢሆን፣ ባዘጋጀሁለት ግብዣ ላይ ንጉሡ ዛሬ ከሐማ ጋር ይገኝልኝ” አለች።
5ንጉሡም፣ “አስቴር ያለችውን እንድንፈጽም፣ ሐማን በፍጥነት ጥሩት” አለ። ስለዚህ ንጉሡና ሐማ አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ ሄዱ። 6የወይን ጠጅ እየጠጡ ሳለ ንጉሡ ዳግመኛ አስቴርን፣ “እስቲ የምትፈልጊው ምንድን ነው? ይሰጥሻል፤ ደግሞስ የምትጠይቂው ምንድን ነው? እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ቢሆን ይፈቀድልሻል” አላት። 7አስቴርም እንዲህ ስትል መለሰች፤ “ልመናዬም፣ ጥያቄዬም ይህ ነው፤ 8በንጉሡ ዘንድ ሞገስ ካገኘሁና የምፈልገውን ሊሰጠኝና ልመናዬንም ሊፈጽምልኝ ንጉሡን ደስ ካሰኘው፣ ንጉሡና ሐማ በማዘጋጅላቸው ግብዣ ላይ ነገ ይገኙልኝ። ከዚያም እኔ ለንጉሡ ጥያቄ መልስ እሰጣለሁ።”
ሐማ በመርዶክዮስ ላይ ያወረደው ቍጣ
9ሐማ በዚያን ቀን ደስ ብሎትና መንፈሱ ረክቶ ወጣ፤ ነገር ግን መርዶክዮስን በንጉሡ በር ላይ ሲያየው ከተቀመጠበት አለመነሣቱንና በፊቱም አለመንቀጥቀጡን ሲመለከት፣ ቍጣው በመርዶክዮስ ላይ ነደደ። 10ሐማ ግን እንደ ምንም ራሱን ተቈጣጥሮ ወደ ቤቱ ሄደ።
ወዳጆቹንና ሚስቱን ዞሳራን አስጠርቶ በአንድነት ከሰበሰባቸው በኋላ፣ 11ሐማ ስለ ሀብቱ ታላቅነት፣ ስለ ልጆቹ ብዛት እንዲሁም ንጉሡ የቱን ያህል እንዳከበረው፣ ከሌሎቹም መኳንንትና ሹማምት ይበልጥ እንዴት ከፍ ከፍ እንዳደረገው እያጋነነ ነገራቸው። 12ሐማም፣ “ምን ይህ ብቻ” አለ፤ “ንግሥት አስቴር ባዘጋጀችው ግብዣ ላይ ከንጉሡ ጋር እንድገኝ የጋበዘችው ሰው አንድ እኔ ብቻ ነኝ፤ ነገም ከንጉሡ ጋር ጋብዛኛለች። 13ነገር ግን አይሁዳዊው መርዶክዮስ በንጉሡ በር ላይ ተቀምጦ ካየሁት ይህ ሁሉ እኔን ደስ አያሰኘኝም።”
14ሚስቱ ዞሳራና ወዳጆቹ በሙሉ፣ “ቁመቱ አምሳ ክንድ#5፥14 23 ሜትር ያህል ነው። የሆነ መስቀያ አስተክልና መርዶክዮስ እንዲሰቀልበት በጧት ለንጉሡ ንገረው፤ ከዚያም ደስ ብሎህ ከንጉሡ ጋር ወደ ግብዣው ግባ” አሉት። ይህም ሐሳብ ሐማን እጅግ ደስ አሰኘው፤ መስቀያውንም አስተከለ።
Currently Selected:
አስቴር 5: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.