መርዶክዮስ የደረሰበትን ነገር ሁሉ፣ እንዲሁም ሐማ የአይሁድን ሕዝብ ለማጥፋት ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት ለማግባት ቃል የገባውን የገንዘብ ልክ ጭምር ነገረው። አይሁድን ለማጥፋት በሱሳ የወጣውን የዋናውን ዐዋጅ ቅጅም ለአስቴር እንዲያሳያትና በዝርዝር እንዲያስረዳት ሰጠው፤ ወደ ንጉሡም ዘንድ ገብታ ስለ ሕዝቧ ምሕረት እንድትጠይቅና እንድትማልድ አጥብቆ ይነግራት ዘንድ አሳሰበው። ሀታክም ተመልሶ መርዶክዮስ የነገረውን ሁሉ ለአስቴር አስታወቃት። እርሷም ለመርዶክዮስ እንዲህ እንዲለው ነገረችው፤ “የንጉሡ ባሮችና በንጉሡ አውራጃዎች የሚገኙ ሰዎች ሁሉ ወንድም ሆነ ሴት፣ ማንም ሰው ሳይጠራ ንጉሡ ወዳለበት ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚገባ፣ ንጉሡ አንድ ሕግ ብቻ እንዳለው ያውቃል፤ ይኸውም እንዲህ ያደረገው ሰው ይገደላል፤ አንድ ሰው ከእንዲህ ዐይነቱ ሞት የሚተርፈው፣ ንጉሡ የወርቅ ዘንጉን ሲዘረጋለት ብቻ ነው። እኔ ግን ወደ ንጉሡ ዘንድ እንድገባ ከተጠራሁ ከሠላሳ ቀን በላይ ሆነ።” የአስቴር ቃል ለመርዶክዮስ በተነገረው ጊዜ፣ ይህን መልስ ላከባት፤ “አንቺ በንጉሥ ቤት በመሆንሽ ብቻ ሌላው የአይሁድ ሕዝብ ሲጠፋ አንቺ የምትተርፊ እንዳይመስልሽ፤ በዚህ ጊዜ አንቺ ዝም ብትዪ፣ ለአይሁድ ርዳታና ትድግና ከሌላ ስፍራ ይመጣላቸዋል፤ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፤ ደግሞስ አንቺ ንግሥት ለመሆን የበቃሽው ለዚህ ጊዜ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?”
አስቴር 4 ያንብቡ
ያዳምጡ አስቴር 4
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አስቴር 4:7-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos