አስቴር 3
3
ሐማ አይሁድን ለማጥፋት የሸረበው ሤራ
1ከዚህም ነገር በኋላ ንጉሥ ጠረክሲስ የአጋጋዊውን የሐመዳቱን ልጅ ሐማን ከፍ ከፍ አደረገው፤ ከሌሎቹም መኳንንት ሁሉ ከፍተኛውን ሥልጣን በመስጠት አከበረው። 2ንጉሡ ስለ እርሱ ይህ እንዲደረግለት አዝዞ ስለ ነበር፣ በንጉሡ በር ያሉት የመንግሥቱ ሹማምት ሁሉ ለሐማ ተንበርክከው እጅ በመንሣት አክብሮታቸውን ይገልጡለት ነበር። መርዶክዮስ ግን ወድቆ አልሰገደለትም፤ አክብሮትም አላሳየውም።
3ታዲያ በንጉሡ በር ያሉት የንጉሡ አገልጋዮች መርዶክዮስን፣ “የንጉሡን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋለህ?” ሲሉ ጠየቁት። 4ይህንም በየቀኑ ይነግሩት ነበር፤ እርሱ ግን አልተቀበላቸውም። አይሁዳዊ መሆኑን ነግሯቸው ስለ ነበር፣ የመርዶክዮስ ባሕርይ እስከ መቼ ሊቀጥል እንደሚችል ለማየት ሲሉ ይህንኑ ለሐማ ነገሩት።
5ሐማም መርዶክዮስ ወድቆ እንዳልሰገደለትና እንዳላከበረው ሲያይ እጅግ ተቈጣ። 6ይልቁንም መርዶክዮስ ከእነማን ወገን መሆኑን በተረዳ ጊዜ፣ መርዶክዮስን ብቻ መግደል እንደ ኢምንት ቈጠረው፤ ስለዚህ ሐማ በመላው የጠረክሲስ መንግሥት ውስጥ የሚገኙትንና የመርዶክዮስ ወገን የሆኑትን አይሁድ ሁሉ ለማጥፋት ዘዴ ፈለገ።
7ንጉሥ ጠረክሲስ በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት ኒሳን በተባለው በመጀመሪያው ወር፣ ቀኑንና ወሩን ለመለየት ፉር የተባለ ዕጣ ሐማ ባለበት ጣሉ፤ ዕጣውም አዳር በተባለው በዐሥራ ሁለተኛው ወር ላይ ወደቀ።
8ከዚያም ሐማ ንጉሥ ጠረክሲስን እንዲህ አለው፤ “በአሕዛብ መካከል በመንግሥትህ አውራጃዎች ሁሉ ተሠራጭቶና ተበታትኖ የሚኖር አንድ ሕዝብ አለ፤ ይህም ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የተለየ ልማድ ያለውና የንጉሡንም ሕግ የማይታዘዝ ነው፤ ታዲያ ይህን ሕዝብ ዝም ማለቱ ለንጉሡ አይበጅም። 9ነገሩ ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ከሆነ፣ እነርሱን ለማጥፋት ዐዋጅ ይውጣ፤ እኔም ይህን ተግባር ለሚፈጽሙ ሰዎች የሚውል ዐሥር ሺሕ መክሊት ብር ወደ መንግሥት ግምጃ ቤት አስገባለሁ።”
10ስለዚህ ንጉሡ የቀለበት ማኅተሙን ከጣቱ አውልቆ የአይሁድ ጠላት ለሆነው ለአጋጋዊው ለሐማዳቱ ልጅ ለሐማ ሰጠው። 11ንጉሡም ሐማን፣ “ገንዘቡን እዚያው ያዘው፤ ሕዝቡንም እንዳሻህ አድርገው” አለው።
12ከዚያም በመጀመሪያው ወር ዐሥራ ሦስተኛው ቀን የንጉሡ ጸሓፊዎች ተጠሩ። እነርሱም የሐማን ትእዛዝ በሙሉ በየአውራጃው ፊደልና በየሕዝቡ ቋንቋ፣ ለንጉሡ እንደራሴዎች፣ ለልዩ ልዩ አውራጃ ገዦችና ለልዩ ልዩ ሕዝቦች መኳንንት ጻፉ። ይህም የተጻፈው በራሱ በንጉሡ ጠረክሲስ ስም ሲሆን፣ የታተመውም በራሱ ማኅተም ነበር። 13አዳር በተባለው በዐሥራ ሁለተኛው ወር፣ በዐሥራ ሦስተኛው ቀን ወጣት፣ ሽማግሌ፣ ሴትና ሕፃን ሳይባል አይሁድ ሁሉ በዚያኑ ዕለት እንዲጠፉ፣ እንዲገደሉና እንዲደመሰሱ፣ ሀብታቸውም እንዲዘረፍ ደብዳቤ ለንጉሡ አውራጃዎች ሁሉ በመልእክተኞች እጅ ተላከ። 14ለእያንዳንዱም አውራጃ ሕዝብ እንዲታወቅ፣ እነርሱም ለዚያ ቀን ዝግጁ እንዲሆኑ፣ የዋናው ዐዋጅ ቅጅ ሕግ እንዲወጣና ወደ እያንዳንዱም አውራጃ እንዲላክ ተደረገ።
15መልእክተኞቹ በንጉሡ ትእዛዝ ተቻኵለው ወጡ፤ ዐዋጁም በሱሳ ግንብ ተላለፈ። ንጉሡና ሐማ ለመጠጣት ተቀመጡ፤ የሱሳ ከተማ ግን ግራ ተጋብታ ነበር።
Currently Selected:
አስቴር 3: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.