እናንተ በበደላችሁና በኀጢአታችሁ ምክንያት ሙታን ነበራችሁ፤ በዚህም፣ የዓለምን ክፉ መንገድ ተከትላችሁ፣ በአየር ላይ ላሉት መንፈሳውያን ኀይላት ገዥ ለሆነውና አሁንም ለእግዚአብሔር በማይታዘዙት ሰዎች ላይ ለሚሠራው መንፈስ እየታዘዛችሁ ትኖሩ ነበር። እኛ ሁላችን በአንድ ወቅት የሥጋችንን ምኞት እያረካን፣ መንገዱንም እየተከተልን በመካከላቸው እንኖር ነበር፤ እንደ ሌሎቹም የቍጣ ልጆች ነበርን። ነገር ግን በምሕረቱ ባለጠጋ የሆነ እግዚአብሔር ለእኛ ካለው ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ፣ በበደላችን ሙታን ሆነን ሳለ፣ በክርስቶስ ሕያዋን አደረገን፤ የዳናችሁት በጸጋ ነው። እግዚአብሔርም ከክርስቶስ ጋር አስነሣን፤ በክርስቶስ ኢየሱስ በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን፤ ይኸውም በሚመጣው ዘመን በክርስቶስ ኢየሱስ በቸርነቱ የገለጠልንን ወደር የሌለውን የጸጋውን ባለጠግነት ያሳይ ዘንድ ነው፤ በእምነት፣ በጸጋ ድናችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ በሥራ አይደለም፤ ምክንያቱም፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀልንን መልካም ሥራ እንድንሠራ በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርን የእግዚአብሔር እጅ ሥራዎች ነን። ስለዚህ እናንተ ቀድሞ በትውልድ አሕዛብ የሆናችሁ፣ በአካል ላይ በሰው እጅ ከተደረገው የተነሣ፣ ራሳቸውን “ተገርዘናል” በሚሉት፣ “ያልተገረዙ” የተባላችሁ ያን አስታውሱ፤ በዚያን ዘመን ከክርስቶስ ተለይታችሁ፣ ከእስራኤል ወገንነት ርቃችሁ፣ ለኪዳኑም ተስፋ ባዕዳን ሆናችሁ፣ በዓለም ላይ ያለ ተስፋና ያለ እግዚአብሔር እንደ ነበራችሁ አስታውሱ። አሁን ግን እናንተ ቀድሞ ርቃችሁ የነበራችሁ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም አማካይነት ቀርባችኋል።
ኤፌሶን 2 ያንብቡ
ያዳምጡ ኤፌሶን 2
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኤፌሶን 2:1-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos