የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መክብብ 1:1-11

መክብብ 1:1-11 NASV

በኢየሩሳሌም የነገሠው፣ የዳዊት ልጅ፣ የሰባኪው ቃል፤ “የከንቱ ከንቱ፤” ይላል ሰባኪው፤ “ሁሉም ነገር ከንቱ፣ የከንቱ ከንቱ ነው።” ከፀሓይ በታች ከሚለፋበት ተግባር ሁሉ፣ ሰው ምን ትርፍ ያገኛል? ትውልድ ይሄዳል፤ ትውልድ ይመጣል፤ ምድር ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች። ፀሓይ ትወጣለች፤ ትጠልቃለችም፤ ወደምትወጣበትም ለመመለስ ትጣደፋለች። ነፋስ ወደ ደቡብ ይነፍሳል፤ ወደ ሰሜንም ይመለሳል፤ ዞሮ ዞሮ ይሄዳል፤ ዘወትርም ወደ ዑደቱ ይመለሳል። ወንዞች ሁሉ ወደ ባሕር ይፈስሳሉ፤ ባሕሩ ግን ፈጽሞ አይሞላም፤ ወንዞች ወደ መጡበት ስፍራ፣ ወደዚያ እንደ ገና ይመለሳሉ። ሰው መናገር ከሚችለው በላይ፣ ነገሮች ሁሉ አድካሚ ናቸው፤ ዐይን ከማየት አይጠግብም፤ ጆሮም በመስማት አይሞላም። የነበረው ነገር እንደ ገና ይሆናል፤ የተደረገውም ተመልሶ ይደረጋል፤ ከፀሓይ በታች ምንም አዲስ ነገር የለም። ማንም፣ “እነሆ፤ ይህ አዲስ ነገር ነው!” ሊል የሚችለው አንዳች ነገር አለን? ቀድሞውኑ በዚሁ የነበረ ነው፤ ከእኛ በፊት የሆነ ነው። የቀድሞ ነገሮች መታሰቢያ የላቸውም፤ ወደ ፊት የሚመጡትም ቢሆኑ፣ ከእነርሱ በኋላ በሚተኩት አይታወሱም።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}