የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘዳግም 31

31
ኢያሱ በሙሴ እግር መተካቱ
1ከዚያም ሙሴ ወጥቶ እነዚህን ቃሎች ለእስራኤል ሁሉ ተናገረ፤ 2“እነሆ፤ መቶ ሃያ ዓመት ሆኖኛል፤ ከእንግዲህ ልወጣና ልገባ አልችልም፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ‘ዮርዳኖስን አትሻገርም’ ብሎኛል፤ 3አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ራሱ በፊትህ ቀድሞ ይሄዳል፤ እነዚህንም አሕዛብ ከፊትህ ያጠፋቸዋል፤ አንተም ምድራቸውን ትወርሳለህ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ተናገረው፣ ኢያሱም አንተን ቀድሞ ይሻገራል። 4እግዚአብሔር (ያህዌ) የአሞራውያንን ነገሥታት ሴዎንንና ዐግን ከነምድራቸው እንዳጠፋቸው፣ እነዚህንም ያጠፋቸዋል። 5እግዚአብሔር (ያህዌ) እነርሱን በፊታችሁ አሳልፎ ይሰጣችኋል፤ እናንተም ያዘዝኋችሁን ሁሉ በእነርሱ ላይ ታደርጋላችሁ። 6ብርቱና ደፋር ሁኑ፤ አትፍሯቸው ወይም አትደንግጡላቸው። አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከአንተ ጋር ይሄዳልና፤ አይተውህም፤ አይጥልህምም።”
7ከዚያም ሙሴ ኢያሱን ጠርቶ በእስራኤል ሁሉ ፊት እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአባቶቻቸው ሊሰጥ ወደ ማለላቸው ምድር ከዚህ ሕዝብ ጋር አብረህ ስለምትገባ፣ ምድሪቱን ርስታቸው አድርገህ ስለምታከፋፍል በርታ፤ ደፋርም ሁን። 8እግዚአብሔር (ያህዌ) ራሱ በፊትህ ይሄዳል፤ ከአንተም ጋር ይሆናል፤ ፈጽሞ አይለይህም፤ አይተውህምም፤ አትፍራ፤ ተስፋም አትቍረጥ።”
ሕጉን ለማንበብ ትእዛዝ ስለ መሰጠቱ
9ሙሴም ይህን ሕግ ጽፎ፣ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) የኪዳን ታቦት ለሚሸከሙ ለሌዊ ልጆች፣ ለካህናቱና ለእስራኤል አለቆች ሁሉ ሰጠ። 10ከዚያም በኋላ ሙሴ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “ዕዳ በሚተውበት፣ የዳስ በዓልም በሚከበርበት፣ በየሰባቱ ዓመት መጨረሻ፣ 11እስራኤል ሁሉ እርሱ በሚመርጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ሲታይ፣ ይህን ሕግ በእነርሱ ፊት በጆሯቸው ታነበዋለህ። 12ይሰሙና አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) መፍራት ይማሩ ዘንድ፣ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ በጥንቃቄ እንዲከተሉ ሕዝቡን ይኸውም ወንዶችን፣ ሴቶችን፣ ልጆችንና በከተሞችህ የሚኖረውንም መጻተኛ ሰብስብ። 13ዮርዳኖስን ተሻግረህ በምትወርሷት ምድር፣ በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ፣ ይህን ሕግ የማያውቁት ልጆቻቸውም መስማትና አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) መፍራት ሊማሩ ይገባቸዋል።”
የእስራኤል አለመታዘዝ አስቀድሞ ስለ መነገሩ
14 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “እነሆ የምትሞትበት ቀን ቀርቧል፤ ትእዛዝ እንድሰጠው ኢያሱን ጥራውና ወደ መገናኛው ድንኳን ቅረቡ።” ሙሴና ኢያሱም ሄዱ፤ ወደ መገናኛው ድንኳንም ቀረቡ።
15 እግዚአብሔርም (ያህዌ) በድንኳኑ ላይ በደመና ዐምድ ተገለጠ፤ የደመናውም ዐምድ ከድንኳኑ ደጃፍ ላይ ቆመ። 16እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፤ ከአባቶችህ ጋር ልታርፍ ነው፤ ይህም ሕዝብ በሚገባበት ምድር በሚገኙ ባዕዳን አማልክት ወዲያውኑ ያመነዝራል። እኔን ይተወኛል፤ ከእነርሱም ጋር የገባሁትን ኪዳን ያፈርሳሉ። 17በዚያች ቀን እቈጣቸዋለሁ፤ እተዋቸዋለሁም፤ ፊቴን ከእነርሱ እሰውራለሁ፤ እነርሱም ይጠፋሉ። ብዙ ጥፋትና የከፋ ችግር ይደርስባቸዋል፤ በዚያችም ቀን፣ ‘ይህ ጥፋት የደረሰብን፣ አምላካችን (ኤሎሂም) ከእኛ ጋር ባለመሆኑ አይደለምን?’ ይላሉ። 18ወደ ባዕዳን አማልክት በመዞር ከፈጸሙት ክፋታቸው የተነሣ፣ በዚያች ቀን ፊቴን ከእነርሱ ፈጽሞ እሰውራለሁ።
19“እንግዲህ ይህን መዝሙር ለራሳችሁ ጻፉ፤ ለእስራኤል ልጆችም አስተምሩ፤ ስለ እኔ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ እንዲዘምሩ አድርጉ። 20ወተትና ማር ወደምታፈስሰውና ለአባቶቻቸው በመሐላ ቃል ወደ ገባሁላቸው ምድር ባመጣኋቸው ጊዜ ከበሉና ከጠገቡ፣ ከበለጸጉም በኋላ፣ እኔን ንቀው ኪዳኔንም አፍርሰው ወደ ባዕዳን አማልክት ይዞራሉ፤ እነርሱንም ያመልካሉ። 21ብዙ ጥፋትና የከፋ ችግር በደረሰባቸው ጊዜ ይህ መዝሙር ምስክር ይሆንባቸዋል፤ በዘሮቻቸው የሚረሳ አይደለምና። ወደ ማልሁላቸው ምድር ሳላስገባቸው በፊት ምን ለማድረግ እንደሚያስቡ እንኳ አስቀድሜ ዐውቃለሁ።” 22ስለዚህም ሙሴ ይህን መዝሙር በዚያች ቀን ጻፈ፤ ለእስራኤላውያንም አስተማራቸው። 23እግዚአብሔርም (ያህዌ) ለነዌ ልጅ ለኢያሱ፣ “በርታ፤ ደፋር ሁን፤ የእስራኤልን ልጆች በመሐላ ቃል ወደ ገባሁላቸው ምድር ታስገባቸዋለህና፤ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ” በማለት ትእዛዝ ሰጠው።
24ሙሴ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የዚህን ሕግ ቃል በመጽሐፍ ጽፎ እንዳበቃ፣ 25የእግዚአብሔርን (ያህዌ) የኪዳን ታቦት የሚሸከሙ ሌዋውያንን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ 26“ይህን የሕግ መጽሐፍ ውሰዱ፤ በእናንተ ላይ ምስክር ሆኖ በዚያ ይኖር ዘንድ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የኪዳን ታቦት አጠገብ አስቀምጡት፤ ይህም በእናንተ ላይ ምስክር ሆኖ በዚያ ይኖራል፤ 27የቱን ያህል ዐመፀኞችና ዐንገተ ደንዳኖች እንደ ሆናችሁ ዐውቃለሁና። እኔ በሕይወት ከእናንተ ጋር እያለሁ እንደዚህ ካመፃችሁ፣ ከሞትሁ በኋላማ የቱን ያህል ልታምፁ! 28ይህን ቃል ይሰሙ ዘንድ እንድናገር፣ ሰማይንና ምድርን ምስክር አድርጌ እንድጠራባቸው፣ የነገድ አለቆቻችሁን በሙሉና ሹሞቻችሁን ሁሉ በፊቴ ሰብስቡ። 29እኔ ከሞትሁ በኋላ ፈጽማችሁ እንደምትረክሱ፣ ካዘዝኋችሁም መንገድ ዘወር እንደምትሉ ዐውቃለሁና። በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ክፉ ድርጊት ስለምትፈጽሙ፣ እጆቻችሁ በሠሯቸውም ነገሮች እርሱን ለቍጣ ስለምታነሣሡት፣ በሚመጡት ዘመናት ጥፋት ይደርስባችኋል።”
የሙሴ መዝሙር
30ሙሴም የዚህን መዝሙር ቃል ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ፣ ለተሰበሰበው የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ በጆሯቸው እንዲህ ሲል አሰማ፤

Currently Selected:

ዘዳግም 31: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ