ዘዳግም 24:1-22

ዘዳግም 24:1-22 NASV

አንድ ሰው አንዲት ሴት ካገባ በኋላ፣ አሳፋሪ ነገር አግኝቶባት ባይደሰትባት፣ የፍች ወረቀት ጽፎ በመስጠት ከቤቱ አስወጥቶ ይስደዳት። ከቤቱ ከወጣች በኋላ ሌላ ባል ብታገባ፣ ሁለተኛ ባሏም እንደዚሁ ጠልቷት የፍች ወረቀት በመስጠት ከቤቱ አስወጥቶ ቢሰድዳት ወይም ቢሞት፣ ከዚያ በኋላ የፈታት የመጀመሪያ ባሏ፣ የረከሰች በመሆኗ እንደ ገና መልሶ ሊያገባት አይችልም፤ ይህ በእግዚአብሔር ፊት አስጸያፊ ነው። አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ላይ ኀጢአት አታምጣ። አዲስ ሚስት በቅርብ ጊዜ ያገባ ሰው፣ ለጦርነት አይሂድ፤ ወይም ሌላ ሥራ እንዲሠራ አይገደድ። ለአንድ ዓመት ነጻ ሆኖ ቤቱ ይቈይ፤ ያገባትን ሚስቱን ደስ ያሰኛት። ወፍጮና መጁን ወይም መጁንም እንኳ ቢሆን፣ የብድር መያዣ አድርገህ አትውሰድ፤ የሰውን ነፍስ መያዣ አድርጎ መውሰድ ይሆናልና። አንድ ሰው ከእስራኤላውያን ወንድሞቹ አንዱን ፈንግሎ በመውሰድ ባሪያ ሲያደርገው ወይም ሲሸጠው ቢገኝ፣ ፈንጋዩ ይሙት። ክፉውን ከመካከልህ አስወግድ። የለምጽ ደዌን በተመለከተ ሌዋውያን ካህናት የሚሰጡህን መመሪያ በትክክል ለመፈጸም ጥንቃቄ አድርግ። እኔ ለእነርሱ የሰጠሁትን ትእዛዝ በጥንቃቄ ተከተል። ከግብጽ ከወጣችሁ በኋላ በመንገድ ላይ ሳላችሁ አምላክህ እግዚአብሔር በማርያም ላይ ያደረገባትን አስታውሱ። ማንኛውንም ነገር ለባልንጀራህ ስታበድር መያዣ አድርጎ የሚሰጥህን ለመቀበል ወደ ቤቱ አትግባ። አንተ ከውጭ ሆነህ ጠብቅ፤ ያበደርኸውም ሰው መያዣውን ከቤት ያምጣልህ። ሰውየው ድኻ ከሆነ፣ መያዣውን ከአንተ ዘንድ አታሳድርበት። መደረቢያውን ለብሶት እንዲያድር ፀሓይ ሳትጠልቅ መልስለት። ከዚያም ያመሰግንሃል፤ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊትም የጽድቅ ሥራ ሆኖ ይቈጠርልሃል። ችግረኛና ድኻ የሆነውን የምንዳ ሠራተኛ እስራኤላዊ ወንድምህም ሆነ፣ ከከተሞችህ በአንዲቱ የሚኖረውን መጻተኛ አትበዝብዘው፤ የሠራበትን ሒሳብ በዕለቱ፣ ፀሓይ ሳትጠልቅ ክፈለው፤ ድኻ በመሆኑ በጕጕት ይጠባበቀዋልና። አለዚያ ወደ እግዚአብሔር ይጮኽና ኀጢአት ይሆንብሃል። አባቶች በልጆቻቸው፣ ልጆችም በአባቶቻቸው አይገደሉ፤ እያንዳንዱ በራሱ ኀጢአት ይገደል። ለመጻተኛው ወይም አባት ለሌለው ልጅ ፍትሕ አትንፈገው፤ የመበለቲቱንም መደረቢያ መያዣ አታድርግ። አንተም በግብጽ ባሪያ እንደ ነበርህና አምላክህ እግዚአብሔር ከዚያ እንደ ተቤዠህ አስታውስ፤ ይህን እንድታደርግ ያዘዝሁህ ለዚህ ነው። የዕርሻህን ሰብል በምታጭድበት ጊዜ፣ ተረስቶ የቀረ ነዶ ቢኖር፣ ያን ለመውሰድ ተመልሰህ አትሂድ። አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ ሥራ ሁሉ እንዲባርክህ ነዶውን ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ተወው። የወይራ ዛፍህን ፍሬ በምታራግፍበት ጊዜ፣ በየቅርንጫፉ ላይ የቀረውን ለመቃረም ተመልሰህ አትሂድ፤ ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ተወው። የወይን ተክልህን ፍሬ ስትሰበስብ ቃርሚያውን ለመሰብሰብ አትመለስበት፤ የቀረውን ለመጻተኛው፣ አባት ለሌለውና ለመበለቲቱ ተወው። በግብጽ ባሪያ እንደ ነበርህ አስታውስ፤ ይህን እንድታደርግ ያዘዝሁህ ለዚህ ነው።