ዘዳግም 13
13
ሌሎች አማልክትን ማምለክ
1ነቢይ ወይም ሕልም ዐላሚ ከመካከልህ ተነሥቶ ምልክት ወይም ድንቅ አደርጋለሁ ቢልህ፣ 2የተናገረው ምልክት ወይም ድንቅ ቢፈጸም፣ “አንተ የማታውቃቸውን ሌሎች አማልክት እናምልካቸው” ቢልህ፣ 3አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በፍጹም ልባችሁና በፍጹም ነፍሳችሁ ትወድዱት እንደ ሆነ ያውቅ ዘንድ ሊፈትናችሁ ነውና፣ የዚያን ነቢይ ቃል ወይም ሕልም ዐላሚውን አትስማ። 4አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ተከተሉት፤ ፍሩት፤ ትእዛዞቹንም ጠብቁ፤ ታዘዙት፤ አገልግሉት፤ ከእርሱም ጋር ተጣበቁ። 5ከግብፅ ባወጣችሁና ከባርነት ምድር በዋጃችሁ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ላይ እንድታምፁ ተናግሯልና፣ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እንድትከተሉት ካዘዛችሁ መንገድ እንድትመለሱ አድርጓልና፣ ያ ነቢይ ወይም ሕልም ዐላሚ ይገደል፤ ስለዚህ ክፉውን ከመካከልህ አስወግድ።
6የእናትህ ልጅ ወንድምህ፣ ወንድ ወይም ሴት ልጅህ፣ ወይም የምትወድዳት ሚስትህ ወይም የልብ ጓደኛህ፣ (አንተም ሆንህ አባቶችህ የማታውቋቸውን አማልክት) “ሄደን ሌሎችን አማልክት እናምልክ” ብሎ በስውር ሊያስትህ ቢሞክር፣ 7በቅርብም ሆነ በሩቅ፣ ከአንዱ የምድር ጫፍ እስከ ሌላው ድረስ በዙሪያህ ያሉትን የአሕዛብ አማልክት እናምልክ ቢልህ፣ 8እሺ አትበለው፤ ወይም አታዳምጠው፤ አትራራለት፤ አትማረው፤ ወይም አትሸሽገው። 9ያለማመንታት ግደለው፤ እርሱንም ለመግደል በመጀመሪያ የአንተ እጅ፣ ከዚያም በኋላ የሕዝቡ ሁሉ እጅ ይነሣ። 10የባርነት ምድር ከሆነው ከግብፅ ካወጣህ ከአምላክህ ከእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሊያርቅህ ፈልጓልና እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ውገረው። 11ከዚያም እስራኤል ሁሉ ሰምተው ይፈራሉ፤ ከመካከልህም ማንም እንደዚህ ያለውን ክፉ ነገር ዳግም አያደርግም።
12አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እንድትኖርባቸው ከሚሰጥህ ከተሞች በአንዲቱ ውስጥ እንዲህ ሲባል ብትሰማ፣ 13ክፉ ሰዎች ከመካከላችሁ ተነሥተው አንተ የማታውቃቸውን፣ “ሌሎች አማልክትን ሄደን እናምልክ” በማለት የከተማቸውን ሕዝብ እያሳቱ ቢሆን፣ 14ጕዳዩን አጣራ፤ መርምር፤ በሚገባም ተከታተል፤ ነገሩ እውነት ሆኖ ከተገኘና ይህ አስጸያፊ ነገር በመካከልህ መፈጸሙ ከተረጋገጠ፣ 15በዚያች ከተማ የሚኖሩትን ሁሉ በሰይፍ ግደላቸው፤ ከተማዪቱን ከነሕዝቧና ከነቀንድ ከብቷ ፈጽሞ ደምስሳት#13፥15 የዕብራይስጡ ቃል አንድን ነገር ወይም አንድን ሰው ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ለእግዚአብሔር መስጠትን የሚያሳይ ነው።። 16በከተማዪቱ የተገኘውን የምርኮ ዕቃ ሁሉ በአደባባይዋ መካከል ላይ ሰብስበህ፣ ከተማዪቱን ከነምርኮዋ እንዳለ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚቀርብ መሥዋዕት አድርገህ በሙሉ አቃጥል። ለዘላለም እንደ ፈረሰች ትቅር፤ ተመልሳም አትሠራ። 17እግዚአብሔር (ያህዌ) ከብርቱ ቍጣው ይመለስ ዘንድ ዕርም ነገሮች በእጅህ አይገኙ#13፥17 የዕብራይስጡ ቃል አንድን ነገር ወይም አንድን ሰው ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ለእግዚአብሔር መስጠትን የሚያሳይ ነው።፤ እርሱ ምሕረቱን ያሳይሃል፤ ይራራልሃል፤ ለአባቶችህ በመሐላ ተስፋ በሰጠው መሠረት ቍጥርህን ያበዛዋል፤ 18ይህም የሚሆነው ዛሬ እኔ የምሰጥህን ትእዛዞቹን ሁሉ በመጠበቅና መልካም የሆነውን በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት በማድረግ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ስለ ታዘዝህለት ነው።
Currently Selected:
ዘዳግም 13: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.