የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዳንኤል 9:3-19

ዳንኤል 9:3-19 NASV

ስለዚህ ማቅ ለብሼ፣ በራሴም ላይ ዐመድ ነስንሼ፣ በጾምና በጸሎት፣ በምልጃም ፊቴን ወደ ጌታ አምላክ አቀናሁ። ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብዬ ጸለይሁ፤ ተናዘዝሁም፤ “ከሚወድዱህና ትእዛዝህን ከሚፈጽሙ ሁሉ ጋር የፍቅር ቃል ኪዳንህን የምትጠብቅ፣ ታላቅና የተፈራህ አምላክ፤ ጌታ ሆይ፤ እኛ ኀጢአት ሠርተናል፤ በድለናልም፤ ክፋትን አድርገናል፤ ዐምፀናልም፤ ከትእዛዝህና ከሕግህ ዘወር ብለናል። ለንጉሦቻችን፣ ለልዑሎቻችንና ለአባቶቻችን እንዲሁም ለምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ በአንተ ስም የተናገሩትን አገልጋዮችህን ነቢያትን አልሰማንም። “ጌታ ሆይ፤ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ነገር ግን ለአንተ ታማኞች ባለመሆናችን እኛን በበተንህባቸው አገሮች ሁሉ የምንገኝ የይሁዳ ሰዎች፣ የኢየሩሳሌምና የመላው እስራኤል ሕዝብ፣ በሩቅም ሆነ በቅርብ ያለን በዚህ ቀን በኀፍረት ተከናንበናል። እግዚአብሔር ሆይ፤ እኛና ንጉሦቻችን፣ ልዑሎቻችንና አባቶቻችን በአንተ ላይ ኀጢአት ስለ ሠራን በኀፍረት ተከናንበናል። ምንም እንኳ በእርሱ ላይ ያመፅን ብንሆን፣ ጌታ አምላካችን ይቅር ባይና መሓሪ ነው። እግዚአብሔር አምላካችንን አልታዘዝነውም፤ ደግሞም በአገልጋዮቹ በነቢያት በኩል የሰጠንን ሕግ አልጠበቅንም፤ መላው እስራኤል አንተን ባለመታዘዝ ሕግህን ተላልፏል፤ ዘወርም ብሏል። “በአንተ ላይ ኀጢአትን ስለ ሠራን፣ በእግዚአብሔር አገልጋይ በሙሴ ሕግ የተጻፈው መሐላና ርግማን ፈሰሰብን። ታላቅ ጥፋት በእኛ ላይ በማምጣት፣ በእኛና በገዦቻችን ላይ የተነገረውን ቃል ፈጸምህብን፤ በኢየሩሳሌም ላይ የተደረገውን የሚያህል ከሰማይ በታች ከቶ የለም። በሙሴም ሕግ እንደ ተጻፈው፣ ይህ ሁሉ ጥፋት በእኛ ላይ ደረሰ፤ ሆኖም ከኀጢአታችን በመመለስና እውነትህን በመከተል ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ምሕረትን አልፈለግንም፤ አምላካችን እግዚአብሔር በሚያደርገው ሁሉ ጻድቅ ነውና፣ በእኛ ላይ እግዚአብሔር ጥፋት ከማምጣት አልተመለሰም፤ እኛም አልታዘዝነውም። “አሁንም ሕዝብህን ከግብፅ ምድር በብርቱ እጅ ያወጣህ፣ እስከዚህም ቀን ድረስ ስምህ እንዲታወቅ ያደረግህ፣ ጌታ አምላካችን ሆይ፤ እኛ ኀጢአትን ሠርተናል፤ አንተንም በድለናል። ጌታ ሆይ፤ ቀድሞ እንዳደረግኸው የጽድቅ ሥራህ ሁሉ፣ ከከተማህ ከኢየሩሳሌም፣ ከቅዱሱም ተራራህ ቍጣህን መልስ፤ በእኛ ኀጢአትና በአባቶቻችን በደል ምክንያት ኢየሩሳሌምና ሕዝብህ በዙሪያችን ባሉት ዘንድ መሣለቂያ ሆነዋል። “አሁንም አምላካችን ሆይ፤ የአገልጋይህን ጸሎትና ልመና ስማ። ጌታ ሆይ፤ ስለ ስምህ ስትል ፊትህን ወደ ፈረሰው መቅደስ መልስ። አምላክ ሆይ፤ ጆሮህን አዘንብለህ ስማ፤ ዐይንህን ገልጠህ መጥፋታችንንና ስምህ የተጠራበትን ከተማ ተመልከት። ልመናችንን የምናቀርበው ስለ ጽድቃችን ሳይሆን፣ ስለ ታላቅ ምሕረትህ ነው። ጌታ ሆይ፤ አድምጥ! ጌታ ሆይ፤ ይቅር በል! ጌታ ሆይ፤ ስማ! አድርግም! ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቷልና፣ አምላኬ ሆይ፤ ስለ ስምህ ስትል አትዘግይ።”