የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዳንኤል 8

8
ዳንኤል በራእዩ ያየው አውራ በግና ፍየል
1ንጉሥ ቤልሻዛር በነገሠ በሦስተኛው ዓመት፣ አስቀድሞ ከተገለጠልኝ ራእይ በኋላ እኔ ዳንኤል ሌላ ራእይ አየሁ። 2በራእዩም፣ በኤላም አውራጃ በሱሳ ግንብ ራሴን አየሁት፤ በራእዩም በኡባል ወንዝ አጠገብ ነበርሁ። 3ዐይኔን አንሥቼ ስመለከት እነሆ፤ ሁለት ቀንዶች ያሉት አውራ በግ በወንዙ አጠገብ ቆሞ አየሁ፤ ቀንዶቹም ረዣዥሞች ነበሩ፤ ከቀንዶቹም አንዱ ከሌላው ይረዝማል፤ የበቀለው ግን ዘግይቶ ነበር። 4አውራ በጉም ወደ ምዕራብ፣ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ በቀንዱ ሲጐሽም አየሁ። ምንም ዐይነት እንስሳ ሊቋቋመው አልቻለም፤ ከእጁም ሊያድን የሚችል አልነበረም፤ የፈለገውን ሁሉ አደረገ፤ ታላቅም ሆነ።
5ስለዚህም ነገር እያሰብሁ ሳለሁ፣ በዐይኖቹ መካከል ትልቅ ቀንድ ያለው አውራ ፍየል፣ መሬት ሳይነካ ምድርን ሁሉ እያቋረጠ በድንገት ከምዕራብ መጣ። 6በወንዙ አጠገብ ቆሞ ወዳየሁት፣ ሁለት ቀንድ ወዳለው አውራ በግ ተንደርድሮ መጣበት፤ በታላቅ ቍጣም መታው፤ 7እየወጋውና ሁለቱን ቀንዶቹን እየሰበረ፣ በጭካኔ አውራውን በግ ሲጐዳ አየሁ፤ አውራ በጉም ለመቋቋም ጕልበት አልነበረውም። ፍየሉ በምድር ላይ ጥሎ ረገጠው፤ አውራ በጉንም ከፍየሉ እጅ ለማዳን የሚችል አልነበረም። 8ፍየሉም ታላቅ ሆነ፤ ነገር ግን በኀይሉ በበረታ ጊዜ፣ ትልቁ ቀንዱ ተሰበረ፤ በቦታውም ወደ አራቱ የሰማይ ነፋሳት የሚያመለክቱ አራት ታላላቅ ቀንዶች በቀሉ።
9ከእነዚህም ቀንዶች መካከል በአንዱ ላይ አንድ ሌላ ትንሽ ቀንድ በቀለ፤ ወደ ደቡብ፣ ወደ ምሥራቅና ወደ መልካሚቱ ምድር በኀይል አደገ። 10ወደ ሰማይ ሰራዊት እስኪደርስ ድረስ አደገ፤ ከከዋክብት ሰራዊትም የተወሰኑትን ወደ ምድር ጣለ፤ ረጋገጣቸውም። 11ከሰማይ ሰራዊት አለቃ ጋር እስኪተካከል ድረስ ራሱን ከፍ ከፍ አደረገ፤ የልዑሉንም የዘወትር መሥዋዕት ወሰደበት፤ የመቅደሱንም ስፍራ አረከሰ። 12ከዐመፅ የተነሣም የቅዱሳን ሰራዊት#8፥12 ወይም ከዐመፅ…ሰራዊቱ ከዘወትሩ መሥዋዕት ጋር ለእርሱ ዐልፎ ተሰጠ፤ የሚያደርገው ሁሉ ተከናወነለት፤ እውነትም ወደ ምድር ተጣለች።
13ከቅዱሳኑም አንዱ ሲናገር ሰማሁ፤ ሌላውም ቅዱስ እንዲህ አለው፤ “ስለ ዘወትሩ መሥዋዕት፣ ለጥፋት ምክንያት ስለ ሆነው ዐመፅ፣ ከእግር በታች እንዲረገጡ ዐልፈው ስለሚሰጡት መቅደስና ሰራዊት የታየው ራእይ የሚፈጸመው መቼ ነው?”
14እርሱም፣ “እስከ ሁለት ሺሕ ሦስት መቶ ምሽቶችና ማለዳዎች ድረስ ይቈያል፤ ከዚያም መቅደሱ እንደ ገና ይነጻል” አለኝ።
የራእዩ ትርጓሜ
15እኔ ዳንኤል ራእዩን ስመለከትና ሳስተውል ሳለ፣ ሰውን የሚመስል ከፊት ለፊቴ ቆመ፤ 16ከኡባልም፣ “ገብርኤል ሆይ፤ ለዚህ ሰው የራእዩን ትርጕም ንገረው” ብሎ የሚጮኽ የሰው ድምፅ ሰማሁ።
17እኔ ወደ ቆምሁበት ስፍራ እየቀረበ ሲመጣ፣ ደንግጬ በግምባሬ ተደፋሁ፤ እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ራእዩ ስለ ዘመኑ ፍጻሜ እንደ ሆነ አስተውል” አለኝ።
18እየተናገረኝ ሳለ፣ በምድር ላይ በግንባሬ ተደፋሁ፤ በከባድ እንቅልፍም ተዋጥሁ፤ እርሱ ግን ዳሰሰኝና በእግሮቼ አቆመኝ።
19እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “ራእዩ በመጨረሻው ዘመን#8፥19 ወይም መጨረሻው በተወሰነው ጊዜ ስለሚሆን ሊሆን ያለውን የሚያመለክት ስለሆነ፣ በኋላ በቍጣው ዘመን ምን እንደሚሆን እነግርሃለሁ፤ 20ያየኸው ሁለት ቀንዶች የነበሩት አውራ በግ፣ የሜዶንና የፋርስን መንግሥታት ያመለክታል። 21ጠጕራሙ ፍየል የግሪክ ንጉሥ ሲሆን፣ በዐይኖቹም መካከል ያለው ትልቁ ቀንድ የመጀመሪያው ንጉሥ ነው። 22የተሰበረውን ቀንድ የተኩት አራቱ ቀንዶች፣ ከመንግሥቱ የሚወጡትን አራት መንግሥታት ያመለክታሉ፤ ነገር ግን በኀይል አይተካከሉትም።
23“በዘመነ መንግሥታቸው በስተ መጨረሻ፣ ዐመፀኞች ፍጹም እየከፉ በሚሄዱበት ጊዜ፣ አስፈሪ ፊት ያለው አታላይ ንጉሥ ይነሣል። 24እጅግ ብርቱ ይሆናል፤ ነገር ግን በገዛ ኀይሉ አይደለም። አሠቃቂ ጥፋት ይፈጽማል፤ የሚያደርገው ሁሉ ይከናወንለታል፤ ኀያላን ሰዎችንና ቅዱሳኑን ሕዝብ ያጠፋል። 25እያጭበረበረ ይበለጽጋል፤ ራሱንም ታላቅ አድርጎ ይቈጥራል። በሰላም ተደላድለን ተቀምጠናል ሲሉ፣ ብዙዎችን ያጠፋል፤ በልዑላን ልዑልም ላይ ይነሣል፤ ይሁን እንጂ እርሱም ይጠፋል፤ ነገር ግን በሰው ኀይል አይደለም።
26“የተሰጠህ የምሽቱና የማለዳው ራእይ እውነት ነው፤ ነገር ግን ከብዙ ዘመን በኋላ የሚሆነውን ስለሚያመለክት ራእዩን ዝጋው።”
27እኔ ዳንኤል ዐቅሜ ተሟጥጦ ነበር፤ ለብዙ ቀናት ታመምሁ፤ ተኛሁም። ከዚያም በኋላ ተነሥቼ ወደ ንጉሡ ሥራ ሄድሁ። ባየሁት ራእይ ተደናግጬ ነበር፤ ነገሩም አልገባኝም።

Currently Selected:

ዳንኤል 8: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ