ዳንኤል 6:1-28

ዳንኤል 6:1-28 NASV

ዳርዮስ በመንግሥቱ ሁሉ ላይ እንዲገዙ አንድ መቶ ሃያ መሳፍንትን መሾም ፈለገ፤ በእነዚህም ላይ ሦስት የበላይ አስተዳዳሪዎችን አደረገ፤ ከእነርሱም አንዱ ዳንኤል ነበረ። ንጉሡ ጕዳት እንዳይደርስበት፣ መሳፍንቱ ተጠሪነታቸው ለሦስቱ የበላይ አስተዳዳሪዎች እንዲሆን ተደረገ። ከመሳፍንቱና ከበላይ አስተዳዳሪዎቹ ሁሉ ይልቅ ዳንኤል ልዩ የጥበብ መንፈስ የሞላበት ሆኖ በመገኘቱ፣ ንጉሡ በመላው ግዛቱ ላይ ሊሾመው ዐሰበ። በዚህ ምክንያት የበላይ አስተዳዳሪዎቹና መሳፍንቱ ዳንኤል በሚያከናውነው የመንግሥት ሥራ ሊከስሱት ሰበብ ፈለጉ፤ ነገር ግን አላገኙበትም፤ ዳንኤል ታማኝ፣ ጠንቃቃና በሥራው እንከን የሌለበት ስለ ነበር፣ በርሱ ላይ ስሕተት ሊያገኙ አልቻሉም። እነዚህም ሰዎች፣ “ከአምላኩ ሕግ ጋራ በተያያዘ ጕዳይ ካልሆነ በቀር፣ ይህን ዳንኤልን የምንከስበት ምንም ሰበብ አናገኝበትም” አሉ። ከዚያም የበላይ አስተዳዳሪዎቹና መሳፍንቱ በአንድነት ወደ ንጉሡ ሄደው እንዲህ አሉ፤ “ንጉሥ ዳርዮስ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ! ንጉሥ ሆይ፤ እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ማንም ሰው ወደ ሌላ ሰውም ሆነ ወደ ሌላ አምላክ መጸለይ እንደሌለበት ንጉሡ ዐዋጅ እንዲያወጣ፣ ትእዛዙም እንዲፈጸም፣ ይህንም የተላለፈ ወደ አንበሶች ጕድጓድ እንዲጣል፣ የመንግሥት የበላይ አስተዳዳሪዎች፣ መኳንንት፣ መሳፍንት፣ አማካሪዎችና አገረ ገዦች ሁሉ በአንድነት ተስማምተዋል። ንጉሥ ሆይ፤ ይህን ዐዋጅ አውጣ፤ እንደማይሻረውና እንደማይለወጠው የሜዶንና የፋርስ ሕግ እንዲሆን ትእዛዙን በጽሑፍ አድርገው።” ስለዚህ ንጉሥ ዳርዮስ ዐዋጁ ተጽፎ እንዲወጣ አደረገ። ዳንኤልም ዐዋጁ እንደ ወጣ ባወቀ ጊዜ ወደ ቤቱ ሄደ፤ መስኮቶቹ በኢየሩሳሌም አንጻር ተከፍተው ባሉበት በሰገነቱ ቀድሞ ያደርግ እንደ ነበረው በቀን ሦስት ጊዜ ተንበርክኮ ጸለየ፤ አምላኩንም አመሰገነ። ሰዎቹም በአንድ ላይ ሄደው፣ ዳንኤልን ሲጸልይና አምላኩን ሲማፀን አገኙት። ወደ ንጉሡም ሄደው፣ “ንጉሥ ሆይ፤ በሚቀጥሉት ሠላሳ ቀናት ማንም ሰው ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ወደ ሰውም ሆነ ወደ ማንኛውም አምላክ ቢጸልይ፣ በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ እንደሚጣል ዐዋጅ አውጥተህ አልነበረምን?” ሲሉ እርሱ ስላወጣው ዐዋጅ ጠየቁት። ንጉሡም፣ “ዐዋጁ እንደማይሻረው እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ የጸና ነው” ሲል መለሰ። እነርሱም ንጉሡን፣ “ንጉሥ ሆይ፤ ከይሁዳ ምርኮኞች አንዱ የሆነው ዳንኤል፣ አንተንም ሆነ በጽሑፍ ያወጣኸውን ዐዋጅ አያከብርም፤ አሁንም በቀን ሦስት ጊዜ ወደ አምላኩ ይጸልያል” አሉት። ንጉሡ ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ዐዘነ፤ ዳንኤልን ለማዳን ወሰነ፤ ፀሓይ እስክትጠልቅም ድረስ የተቻለውን ሁሉ አደረገ። ከዚያም ሰዎቹ በአንድ ላይ ወደ ንጉሡ ቀርበው፣ “ንጉሥ ሆይ፤ በሜዶንና በፋርስ ሕግ መሠረት፣ አንድ ንጉሥ ያወጣው ዐዋጅም ሆነ ትእዛዝ ሊለወጥ እንደማይችል ዕወቅ” አሉት። ስለዚህ ንጉሡ ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም ዳንኤልን አመጡት፤ ወደ አንበሶችም ጕድጓድ ጣሉት። ንጉሡም ዳንኤልን፣ “ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ ያድንህ!” አለው። ድንጋይ አምጥተው በጕድጓዱ አፍ ላይ ገጠሙበት፤ ንጉሡም፣ በዳንኤል ላይ የተፈጸመው እንዳይለወጥ በራሱ የቀለበት ማኅተምና በመሳፍንቱ ቀለበቶች ዐተመበት። ንጉሡም ወደ ቤተ መንግሥቱ ተመለሰ፤ በዚያም ሌሊት ምግብ ሳይበላ፣ የሚያዝናናውም ነገር ሳይቀርብለት ዐደረ፤ እንቅልፍም ከርሱ ራቀ። በማለዳም ገና ጎሕ ሲቀድ፤ ንጉሡ ተነሥቶ ወደ አንበሶቹ ጕድጓድ እየተጣደፈ ሄደ። ወደ ጕድጓዱም ቀርቦ በሐዘን ድምፅ ዳንኤልን፣ “የሕያው አምላክ አገልጋይ ዳንኤል ሆይ፤ ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ ከአንበሶቹ ሊያድንህ ችሏልን?” ብሎ ተጣራ። ዳንኤልም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ፤ ንጉሥ ሆይ፤ በፊቱ ቅን ሆኜ ስለ ተገኘሁ፣ በአንተም ፊት በደል ስላልተገኘብኝ፣ አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶቹን አፍ ዘጋ፤ እነርሱም አልጐዱኝም።” ንጉሡ እጅግ ተደስቶ፤ ዳንኤልን ከጕድጓዱ እንዲያወጡት አዘዘ። ዳንኤል በአምላኩ ታምኖ ነበርና ከጕድጓድ በወጣ ጊዜ፣ አንዳች ጕዳት አልተገኘበትም። በንጉሡ ትእዛዝ፣ ዳንኤልን በሐሰት የከሰሱትን ሰዎች፣ ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋራ አምጥተው፣ በአንበሶቹ ጕድጓድ ውስጥ ጣሏቸው፤ ገና ወደ ጕድጓዱ መጨረሻ ሳይደርሱም፣ አንበሶቹ ቦጫጨቋቸው፤ ዐጥንቶቻቸውንም ሁሉ ሰባበሩ። ከዚያ በኋላ ንጉሥ ዳርዮስ፣ በምድር ላይ ለሚኖሩ ሕዝቦች፣ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎች ሁሉ እንዲህ የሚል መልእክት ጻፈ፤ “ሰላም ይብዛላችሁ! “በማንኛውም የመንግሥቴ ግዛት ሰው ሁሉ፣ የዳንኤልን አምላክ እንዲፈራና እንዲያከብር ይህን ዐዋጅ አውጥቻለሁ። “እርሱ ለዘላለም የሚኖር፣ ሕያው አምላክ ነውና፣ መንግሥቱ አይጠፋም፤ ለግዛቱም መጨረሻ የለውም። እርሱ ይታደጋል፤ ያድናልም፤ በሰማይና በምድር፣ ምልክቶችንና ድንቆችን ያደርጋል፤ ዳንኤልን፣ ከአንበሶች አፍ አድኖታል።” ስለዚህ ዳንኤል በዳርዮስ ዘመነ መንግሥትና በፋርሳዊው በቂሮስ ዘመነ መንግሥት ሁሉ ኑሮው ተሳካለት።