የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዳንኤል 3:17-30

ዳንኤል 3:17-30 NASV

ንጉሥ ሆይ፤ በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ብንጣል፣ የምናመልከው አምላክ ሊያድነን ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል። ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ ባያድነንም እንኳ፤ አማልክትህን እንደማናገለግል፣ ላቆምኸውም የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ።” ከዚያም ናቡከደነፆር በሲድራቅ፣ በሚሳቅና በአብደናጎ እጅግ ተቈጣ፣ ፊቱም ተለወጠባቸው፤ የእቶኑ እሳትም ቀደም ሲል ከነበረው ሰባት ዕጥፍ ተደርጎ እንዲነድድ አዘዘ። ከሰራዊቱም ብርቱ የሆኑትን ጥቂት ወታደሮች፣ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን አስረው ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ እንዲጥሏቸው አዘዘ። እነርሱም መጐናጸፊያቸውን፣ ሱሪያቸውን፣ የራስ ጥምጥማቸውንና ሌሎች ልብሶቻቸውን እንደ ለበሱ ታስረው በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ተጣሉ። የንጉሡ ትእዛዝ አስቸኳይ ስለ ነበረና የእቶኑም እሳት እጅግ ስለ ነደደ፣ የእሳቱ ወላፈን ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን ወስደው የጣሏቸውን ወታደሮች ገደላቸው። ሦስቱ ሰዎች ግን ተጠፍረው እንደ ታሰሩ በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ወደቁ። ከዚህ በኋላ ንጉሥ ናቡከደነፆር በአድናቆት ከተቀመጠበት ዘልሎ በመነሣት አማካሪዎቹን “አስረን በእሳት ውስጥ የጣልናቸው ሰዎች ሦስት አልነበሩምን?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም፣ “ንጉሥ ሆይ፤ እውነት ነው” አሉ። እርሱም፣ “እነሆ፤ ያልታሰሩና ያልተጐዱ አራት ሰዎች በእሳቱ ውስጥ ሲመላለሱ አያለሁ፤ አራተኛውም የአማልክትን ልጅ ይመስላል” አላቸው። ናቡከደነፆርም ወደሚነድደው የእቶን እሳት በር ቀረብ ብሎ ከፍ ባለ ድምፅ፣ “እናንተ የልዑል አምላክ አገልጋዮች ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብድናጎ፤ ኑ ውጡ! ወደዚህ ኑ!” አላቸው። ስለዚህ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብድናጎ ከእሳቱ ወጡ፤ መኳንንቱ፣ ሹማምቱ፣ አገረ ገዦቹና የቤተ መንግሥት አማካሪዎችም በዙሪያቸው ተሰበሰቡ፤ እነርሱም እሳቱ ሰውነታቸውን እንዳልጐዳ፣ ከራሳቸውም ጠጕር አንዲቷ እንኳ እንዳልተቃጠለች አዩ፤ የመጐናጸፊያቸው መልክ አልተለወጠም፤ የእሳትም ሽታ በላያቸው አልነበረም። ከዚያም ናቡከደነፆር እንዲህ አለ፤ “መልአኩን ልኮ አገልጋዮቹን ያዳነ፣ የሲድራቅ፣ የሚሳቅና የአብደናጎ አምላክ ይባረክ፤ በእርሱ በመታመን የንጉሡን ትእዛዝ ጥሰው፣ ከአምላካቸው በቀር ሌላ አምላክ ለማገልገልም ሆነ ለእርሱ ለመስገድ ፈቃደኛ ባለመሆን ሕይወታቸውን አሳልፈው ሰጥተዋልና። ስለዚህ እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅ፣ በሚሳቅና በአብደናጎ አምላክ ላይ ማናቸውንም ቃል የሚናገሩ ሕዝቦችም ሆኑ ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሁሉ ይቈራረጣሉ፤ ቤቶቻቸውም የፍርስራሽ ክምር ይሆናሉ ብዬ አዝዣለሁ።” ከዚያም ንጉሡ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን በባቢሎን አውራጃ ላይ ሾማቸው።