በጽዮን ተዘልላችሁ የምትቀመጡ፣ በሰማርያ ተራራ ያለ ሥጋት የምትኖሩ፣ የእስራኤልም ሕዝብ ለርዳታ ወደ እናንተ የሚመጡባችሁ፣ እናንተ የአሕዛብ አለቆች ሆይ፤ ወዮላችሁ! ወደ ካልኔ ሂዱ፤ እርሱንም ተመልከቱ፤ ከዚያም ወደ ታላቂቱ ሐማት ሂዱ፤ ወደ ፍልስጥኤም ከተማ ወደ ጋትም ውረዱ፤ እነዚህ ከሁለቱ መንግሥታታችሁ ይሻላሉን? የምድራቸውስ ስፋት ከእናንተ ይበልጣልን? ክፉውን ቀን ለምታርቁ፣ የግፍንም ወንበር ለምታቀርቡ ወዮላችሁ! በዝኆን ጥርስ ባጌጠ ዐልጋ ላይ ለምትተኙ፤ በድንክ ዐልጋችሁ ላይ ለምትዝናኑ፣ ከበጎች መንጋ ጠቦትን፣ ከሠቡትም ጥጃን ለምትበሉ፤ ባልተቃኘ በገና እንደ ዳዊት ለምትዘፍኑ፣ በሙዚቃ መሣሪያ ለመጫወት ለምትሹ፣ በፋጋ የወይን ጠጅ ለምትጠጡ፣ ምርጥ ሽቱም ለምትቀቡ፣ ስለ ዮሴፍ መከራ ግን ለማታዝኑ ወዮላችሁ! ስለዚህ እናንተ በመጀመሪያ በምርኮ ከሚወሰዱት መካከል ናችሁ፤ መፈንጠዛችሁና መዝናናታችሁም ያበቃል። ጌታ እግዚአብሔር “የያዕቆብን ትዕቢት ተጸይፌአለሁ፤ ምሽጎቹንም ጠልቻለሁ፤ ከተማዪቱንና በውስጧ ያለውን ሁሉ፣ አሳልፌ እሰጣለሁ” ሲል በራሱ ምሏል፤ ይላል የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር። በአንድ ቤት ውስጥ ዐሥር ሰዎች ቢቀሩ እነርሱም ይሞታሉ። በድኖቹንም ከቤት አውጥቶ ማቃጠል ያለበት አንድ ዘመድ መጥቶ ተደብቆ ያለውን ሰው፣ “ከአንተ ጋራ የቀረ ሌላ ሰው አለን?” ሲለው፣ እርሱም “የለም” ይለዋል፤ ከዚያም በኋላ፣ “ዝም በል፤ የእግዚአብሔርን ስም መጥራት አይገባንም” ይለዋል። እነሆ፤ እግዚአብሔር ትእዛዝ ሰጥቷልና፤ ታላላቅ ቤቶችን ያወድማቸዋል፤ ትንንሾቹንም ያደቅቃቸዋል። ፈረሶች በጭንጫ ላይ ይሮጣሉን? ሰውስ እዚያ ላይ በበሬ ያርሳልን? እናንተ ግን ፍትሕን ወደ መርዝነት፣ የጽድቅንም ፍሬ ወደ መራራነት ለወጣችሁ። እናንተ ሎዶባርን በማሸነፋችሁ ደስ ያላችሁ፣ “ቃርናይምን በራሳችን ብርታት ይዘናል” የምትሉ። የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፣ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፤ እነሆ፤ እኔ ከሐማት መግቢያ እስከ ዓረባ ሸለቆ ድረስ፣ የሚያስጨንቃችሁን ሕዝብ፣ በእናንተ ላይ አስነሣለሁ።”
አሞጽ 6 ያንብቡ
ያዳምጡ አሞጽ 6
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አሞጽ 6:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች