በቴቁሔ ከነበሩት እረኞች መካከል አንዱ የሆነው አሞጽ፣ ዖዝያን የይሁዳ ንጉሥ በነበረ ጊዜ እንዲሁም የዮአስ ልጅ ኢዮርብዓም የእስራኤል ንጉሥ በነበረ ጊዜ፣ ይኸውም የምድር መናወጥ ከመሆኑ ከሁለት ዓመት በፊት ስለ እስራኤል ያየውና የተናገረው ቃል ይህ ነው፤ እርሱም እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ከጽዮን ድምፁን ከፍ አድርጎ ያሰማል፤ ከኢየሩሳሌምም ያንጐደጕዳል፤ የእረኞች ማሰማሪያዎች ደርቀዋል፤ የቀርሜሎስም ዐናት ጠውልጓል።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ ሦስቱ የደማስቆ ኀጢአት፣ ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቍጣዬን አልመልስም፤ የብረት ጥርስ ባለው ማሄጃ፣ ገለዓድን አሂዳለችና፤ የቤን ሃዳድ ምሽጎች እንዲበላ፣ በአዛሄል ቤት ላይ እሳት እሰድዳለሁ። የደማስቆን በሮች እሰባብራለሁ፤ በቤት ዔደን በትር የያዘውን፣ በአዌን ሸለቆ ያለውን ንጉሥ እደመስሳለሁ፤ የሶርያም ሕዝብ ተማርኮ ወደ ቂር ይሄዳል” ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ ሦስቱ የጋዛ ኀጢአት፣ ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቍጣዬን አልመልስም፤ ሕዝቡን ሁሉ ማርካ በመውሰድ፣ ለኤዶም ሸጣለችና። ምሽጎቿን እንዲበላ፣ በጋዛ ቅጥሮች ላይ እሳት እሰድዳለሁ። በአስቀሎና በትር የያዘውን፣ የአሽዶድንም ንጉሥ እደመስሳለሁ፤ በፍልስጥኤም ካሉት የመጨረሻው ሰው እስኪሞት ድረስ፣ እጄን በአቃሮን ላይ እዘረጋለሁ፤” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ ሦስቱ የጢሮስ ኀጢአት፣ ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቍጣዬን አልመልስም። የወንድማማችነትን ቃል ኪዳን በማፍረስ፣ ሕዝቡን ሁሉ ማርካ ለኤዶም ሸጣለችና። ምሽጎቿን እንዲበላ፣ በጢሮስ ቅጥሮች ላይ እሳት እሰድዳለሁ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ ሦስቱ የኤዶም ኀጢአት፣ ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቍጣዬን አልመልስም፤ ርኅራኄን በመንፈግ፣ ወንድሙን በሰይፍ አሳድዶታልና፤ የቍጣውንም ነበልባል ሳይገድብ፣ መዓቱን ሳያቋርጥ አውርዶበታልና፤ የባሶራን ምሽጎች እንዲበላ፣ በቴማን ቅጥሮች ላይ እሳት እሰድዳለሁ።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ ሦስቱ የአሞን ኀጢአት፣ ይልቁንም ስለ አራቱ፣ ቍጣዬን አልመልስም፤ ድንበሩን ለማስፋት፣ የገለዓድን ነፍሰ ጡር ሴቶች ሆድ ቀድዷልና። በጦርነት ቀን በጩኸት ውስጥ፣ በማዕበል ቀን በዐውሎ ነፋስ ውስጥ፣ ምሽጎቿን እንዲበላ፣ በረባት ቅጥሮች ላይ እሳት እሰድዳለሁ። ንጉሧ ከሹማምቱ ጋራ፣ በአንድነት ተማርኮ ይሄዳል፣” ይላል እግዚአብሔር።
አሞጽ 1 ያንብቡ
ያዳምጡ አሞጽ 1
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አሞጽ 1:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች