ሐዋርያት ሥራ 5:17-42

ሐዋርያት ሥራ 5:17-42 NASV

ከዚህም የተነሣ ሊቀ ካህናቱና ዐብረውት የነበሩት የሰዱቃውያን ወገን ሁሉ በቅናት ተሞሉ፤ ሐዋርያትንም ይዘው ማረፊያ ቤት ከተቷቸው። ይሁን እንጂ የጌታ መልአክ በሌሊት የእስር ቤቱን ደጆች ከፍቶ አወጣቸውና፣ “ሂዱ፤ በቤተ መቅደሱም አደባባይ ቁሙ፤ የዚህንም ሕይወት ቃል ሁሉ ለሕዝብ ንገሩ” አላቸው። እንደ ነጋም፣ በተነገራቸው መሠረት ወደ ቤተ መቅደሱ አደባባይ ገብተው ሕዝቡን ማስተማር ጀመሩ። ሊቀ ካህናቱና ከርሱ ጋራ የነበሩት መጥተው የአይሁድን ሸንጎና የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጉባኤ በሙሉ በአንድነት ሰበሰቡ፤ ሐዋርያትንም እንዲያመጡ ሰዎችን ወደ እስር ቤት ላኩ። አገልጋዮቹም ወደ እስር ቤቱ ሄደው በዚያ አላገኟቸውም፤ ተመልሰውም እንዲህ አሏቸው፤ “እስር ቤቱ በሚገባ ተቈልፎ፣ ጠባቂዎቹም በበሩ ላይ ቆመው አገኘን፤ ከፍተን ስንገባ ግን በውስጡ ማንም አልነበረም።” የቤተ መቅደሱ ጥበቃ ሹምና የካህናት አለቆችም ይህን በሰሙ ጊዜ በነገሩ ተገረሙ፤ ግራም ተጋቡ። በዚህ ጊዜ አንድ ሰው መጥቶ፣ “እነሆ፤ እስር ቤት ያስገባችኋቸው ሰዎች በቤተ መቅደሱ አደባባይ ቆመው ሕዝቡን እያስተማሩ ናቸው” አላቸው። የአገልጋዮቹ ሹሙም ከወታደሮቹ ጋራ ሄዶ፣ ይዞ አመጣቸው፤ ያመጧቸው ግን ሕዝቡ በድንጋይ እንዳይወግሯቸው ስለ ፈሩ በኀይል ሳያስገድዱ ነበር። ሐዋርያትንም አምጥተው በሸንጎው ፊት አቆሟቸው፤ ሊቀ ካህናቱም እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፤ “በዚህ ስም እንዳታስተምሩ በጥብቅ አስጠንቅቀናችሁ ነበር፤ እናንተ ግን ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞላችኋት፤ ደግሞም እኛን ለዚህ ሰው ደም ተጠያቂዎች ልታደርጉን ቈርጣችሁ ተነሣችሁ።” ጴጥሮስና ሌሎች ሐዋርያትም መልሰው እንዲህ አሉ፤ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል! እናንተ በዕንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን፣ የአባቶቻችን አምላክ ከሙታን አስነሣው፤ እርሱም ለእስራኤል ንስሓንና የኀጢአትን ስርየት ይሰጥ ዘንድ፣ እግዚአብሔር የሁሉ ራስና አዳኝ አድርጎ በቀኙ ከፍ ከፍ አደረገው። እኛም ለእነዚህ ነገሮች ምስክር ነን፤ ደግሞም እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምስክር ነው።” ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ ክፉኛ ተቈጡ፤ ሊገድሏቸውም ፈለጉ። ነገር ግን በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ የተከበረ አንድ የሕግ መምህር፣ እርሱም ገማልያል የሚሉት ፈሪሳዊ ተነሥቶ በሸንጎው መካከል ቆመና ሐዋርያትን ወደ ውጭ አውጥተው ለጥቂት ጊዜ እንዲያዩአቸው አዘዘ፤ ለሸንጎውም እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ በእነዚህ ሰዎች ላይ ልታደርጉ ስላሰባችሁት ነገር በጥንቃቄ ልታጤኑ ይገባችኋል። ከዚህ ቀደም፣ ቴዎዳስ ራሱን ትልቅ አድርጎ በመቍጠር ተነሥቶ፣ አራት መቶ ያህል ሰዎች ተባበሩት፤ ነገር ግን እርሱም ተገደለ፤ ተከታዮቹም ሁሉ ተበታተኑ፤ ነገሩም እንዳልነበር ሆነ። ከርሱም በኋላ፣ በሕዝብ ቈጠራው ወቅት ገሊላዊው ይሁዳ ተነሥቶ ብዙ ሕዝብ አሸፈተ፤ ተከታይም አግኝቶ ነበር፤ እርሱም ጠፋ፤ ተከታዮቹም ተበተኑ። ስለዚህ አሁንም የምላችሁ፦ እነዚህን ሰዎች ተዉአቸው! አትንኳቸው! ሐሳባቸው ወይም አድራጎታቸው ከሰው ከሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር ከሆነ ግን ልትገቷቸው አትችሉም፤ እንዲያውም ከእግዚአብሔር ጋራ ስትጣሉ ትገኙ ይሆናል።” እነርሱም ምክሩን ተቀብለው ሐዋርያትን አስጠርተው አስገረፏቸው፤ ዳግመኛም በኢየሱስ ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ለቀቋቸው። ሐዋርያትም፣ ስለ ስሙ ውርደትን ለመቀበል በመብቃታቸው ደስ እያላቸው ከሸንጎው ወጥተው ሄዱ፤ በየዕለቱም፣ በቤተ መቅደስም ሆነ በየቤቱ፣ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ከማስተማርና ከመስበክ ከቶ ወደ ኋላ አላሉም ነበር።